<> Skip to main content
የዓፄ ኃይለሥላሴ መስቀል ከእሳት አደጋ ከተረፉ ቅርሶች አንዱ ሆኗል፡፡

በፈረንሳይ ቃጠሎ በደረሰበት የኖትሬ ዳም ካቴድራል የዓፄ ኃይለሥላሴ ስጦታ መስቀል ከጉዳት ተርፏል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 11/2011ዓ.ም (አብመድ) ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለሥላሴ በ1940ዎቹ አጋማሽ ለፈረንሳዩ ኖትሬ ዳም ካቴድራል በስጦታ ያበረከቱት መስቀል ሰሞኑን ካቴድራሉ ካጋጠመው የእሳት አደጋ ከተረፉ ቅርሶች አንዱ ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን ኃላፊው ኢማኑኤል በስኔር በትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት ከቃጠሎው የተረፈው የንጉሠ ነገሥቱ ስጦታ መስቀል ወደ ሎቭረን ሙዚዬም ተዛውሯል፡፡

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የተቃጠለው ካቴድራል የደረሰበት የጉዳት መጠን ገና እየተጠና ነው፤ በርካታ ሀገራትም የሐዘን መግለጫ ለፈረንሳይ እያደረሱ ነው፡፡

ካቴድራሉ የ850 ዓመታን ታሪክ የያዘና በፓሪስ የሚገኝ የጎብኝዎች መዳረሻ ነበር፡፡ በየዓመቱ 14 ሚሊዮን ጎብኝዎች እንደሚጎበኙትም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቅርስና የገነት ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ እንደነበርም ይጠቀሳል፡፡

የካቴድራሉ 850ኛ ዓመት በዓል በአውሮፓውያኑ 2013 ነበር የተከበረው፤ ይህም በዚህ ዓመት ዕድሜው 856 ዓመት መሆኑን ያመለክታል፡፡ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት ኢማኑኤል ማክሮን በተሻለ ሁኔታ መልሰው እንደሚገነቡት አስታውቀው ነበር፡፡

ምንጭ፡- አፍሪካ ኒውስ

በአብርሃም በዕውቀት

Image