<> Skip to main content
በአማራ ክልል ሦስት ወረዳዎች በአተት በሽታ የ12 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2011ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ጎንደር ዞን የበየዳ እና ጠለምት ወረዳዎች እና በዋግ ኽምራ ብሔረስብ አስተዳደር የአበርገሌ ወረዳ በተፈጠረ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ እስካሁን ባለዉ መረጃ የ12 ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፡፡

Image may contain: text

‹‹የንጹሕ መጠጥ ውኃ ባለመኖሩ ሰዎች የዝናብ ውኃ ከኩሬ እና ከወንዝ በመጠጣታቸው ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ተጋልጠው ሕይወታቸው አልፏል›› በማለት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአበርገሌ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን የበየዳ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ደግሞ ‹‹የዝናብ ውኃን እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ አማራጭ አለመኖሩ ለአተት መስፋፋት እንዳያጋልጥ ሰግተናል›› ብሏል፤ የሕክምና ቁሳቁስ እጥረቶች ስጋት መሆናቸውንም ገልጿል፡፡

በሽታዉ በተከሰተባቸዉ አካባቢዎች የአበርገሌ ወረዳ ደቢ ቀበሌ፣ የበየዳ ወረዳ ጠዘን እና ጓይንት ቀበሌ፣ የጠለምት ወረዳ ቤተል እና በስቂያ ቀበሌ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም ወንድሙ በሽታው የተከሰተዉ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ የዝናብ ውኃ ከኩሬ እና ከወንዝ በመጠጣቱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በሽታዉ የተከሰተበት አካባቢ ሩቅ እና በሽታውም አጣዳፊ በመሆኑ የሕክምና ግብዓቶች እስኪደርሱ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ኃላፊዉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በደቤ ቀበሌ ለበሽታው ተጋላጭ የነበሩ 55 ሰዎችን በጊዜያዊ የሕክምና ቦታ ክትትል በማድረግ ሕይወታቸውን ማትረፍ ተችሏል›› ብለዋል አቶ ሙሉዓለም፡፡ መሠል ችግሮች እንዳይከሰቱ የመከላከያ ስልቶችን እና ውኃን አክመው እንዲጠጡ መድኃኒቶች መሠጠታቸውን ኃላፊዉ ነግረውናል፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን የጠለምት ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለአምላክ ተስፋ ደግሞ ‹‹የበሽታው መነሻ በአንድ ሐዘን ቤት የነበሩ ሰዎች የዝናብ ውኃ መጣታቸው ነው፤ በሽታው 110 ሰዎችን አጥቅቶ የ8 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ከበሽታው አጣዳፊነት ላይ የትራንስፖርት ችግርና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ተዳምሮ መከላከሉን ፈታኝ እንዳደረገው ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ አቶ አለአምላክ እንደተናገሩት ከክልልና ከፌዴራል በመጡ ባለሙያዎች በመታገዝ በተደረገ ጥረት አዲስ በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች እንዳይኖሩ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

‹‹በጠለምት ወረዳ የሚገኙ አምሥት ቆላማ ቀበሌዎች የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የሌላቸው መሆኑ እና ከአንድ ዓመት በላይ የዝናብ እጥረት የነበረባቸው በመሆኑ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ሲገኝ በኩሬ በማስቀረት ለመጠጥ ይጠቀማሉ›› ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የተገኘን ውኃ በመጠጣት የሰው ሕይወት እየጠፋ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
የበየዳ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን መብራት ደግሞ ከሁለት ሳምንት በፊት የተከሰተው የአተት በሽታ ምክንያት የዝናብ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች የመጠጥ ውኃን ከዝናብ ከኩሬና ከወንዝ በመሰብሰብ መጠቀማቸው መሆኑን በመግለጽ መንስኤው በጠለምትና አበርገሌ ወረዳዎች ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በወረዳው በአራት ሰዎች ላይ በሽታው ታይቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰሎሞን ‹‹በመጀመሪያ በበሽታው የተያዘዉ ሰው ሕይወቱ አልፏል፤ ሌሎችን ግን ማትረፍ ችለናል፡፡ አሁንም ግን አተቱ እንዳይከሰት የዝናብ ውኃን እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ አማራጭ ባለመኖሩ እና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረቶች ስላሉ ስጋት አለ›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና እና አደጋዎች መከታተል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አያሌው የአተት በሽታ በተከሰተባቸው ሦስት ወረዳዎች በበቂ መጠን እና ወደፊት ሊከሰት የሚችለውንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ሙሉ የሕክምና ቁሳቁስ መላኩን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የምንልከውን ቁሳቁስ ለማጓጓዝ መኪና መግባት የማይችልባቸው ቦታዎች ስለሆኑ ዞኖች ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ማድረስ ይኖርባቸዋል›› ብለዋል፡፡ በማንኛውም ጊዜ የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ቢገጥማቸው ወረዳዎቹ በጠየቁት ልክ ለመስጠት ግብዓቶቹ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የአተት ወረርሽኙን መቆጣጠር እንዲቻል 205 አባላት ያሉት ፈጣን ምላሽ ሰጭ ቡድን ከፌዴራል፣ ክልልና ዞን ተውጣጥቶ ወደ አካባቢዎቹ መላኩን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በአማራ ክልል በእነዚህ አካባቢዎች የአተት በሽታ ሲከሰት ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም፡፡ ለበሽታው ዘላቂ መፍትሔ ከሕክምና አማራጮች ባለፈ የንጹሕ የመጠጥ ውኃ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ ለወቅታዊ መፍትሔ ውኃን ማከም፣ ማፍላት፣ የበሰሉ ምግቦችን መጠቀም፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በሚገባ በንጹሕ ውኃ አጥቦ መጠቀም፣ መጸዳጃ ቤቶችን በአግባቡ መጠቀም እና የሕክምና ባለሙያዎችን ምክር መከተል እንደሚገባ ይመከራል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.