<> Skip to main content
ነዋሪዎች አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ያሏቸውን ጥያቄዎች አቀረቡ።

የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዎች አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ያሏቸውን ጥያቄዎች ለመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀረቡ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በደብረ ታቦር ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

Image may contain: 10 people, people smiling, crowd

በውይይት መድረኩ የደብረ ታቦር ከተማ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ በአማራ ብሔር ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች፣ የአመራሩ የለውጥ አረዳድና ተያያዥ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ የመብራት፣ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄዎች፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ጥያቄዎችንም ተወያዮቹ ጠይቀዋል፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር፣ የሕገ-መንግሥት መሻሻል፣ የዳሸን ቢራ የማከፋፈል ውክልና እና በየቦታው የሚፈፀም ዘረፋ እንዲቆም ተጠይቋል፡፡

ከተወያዮቹ ለቀረቡ ጥያቄዎችም በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደር፣ የዞንና የክልል መሪዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የፌደራል ውኃ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር በሻህ ሞገሴ የከተማውን የውኃ ችግር አስመልክቶ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የውኃ ችግር መኖሩን መመልከታቸውን ገልጸዉ ‹‹ከክልሉ ውኃ ቢሮ ጋር አንድ አቋም ላይ በመድረስ ከውኃ ልማት ፈንድ እንዴት አድርጎ ለችግሩ አፋጣኝና ዘለቄታዊ ምላሽ እንደሚሰጥ መግባባት ላይ ተደርሷል›› ብለዋል፡፡ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመብራት ችግር ምን ያክል አንገብጋቢ እንደሆነ እና ምላሽ መስጠት ያለበት መሆኑን ለማስገንዘብ መረጃውን ለሚመለከተው አካል እንዲደርስ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ውኃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይመር ሀብቴም ችግሩ መኖሩን አረጋግጠው ለመፍትሔ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይ ኃላፊ አቶ ሸጋው የሻምበል ደግሞ ‹‹ወረታ ያለው ሰብስቴሽ የመቆራረጥ ችግር አለበት›› የሚል ምላሽ ነው የሰጡት፡፡ በመሆኑም አንደ ተቋማቸው ተጨማሪ ሰብስቴሽን ግንባታ መፍትሔ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይህንን ተግባር የሚያከናውነው ኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ ጥያቄውን አቅርበናል፤ ወደፊትም ተፈጻሚ የሚሆንበትን መንገድ እያመቻቸን እንሄዳለን›› ብለዋል፡፡ ከሳምንታት በኋላ የግንባታ ቦታ ርክክብ ለዓለም ባንክም ጭምር ሪፖርት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

የደብረታቦር ከተማ ምክትል ከንቲባ አበበ እምቢያለ በከተማው ውስጥ ያሉ የሠላም እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንደሚፈቱ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ተግባርም የከተማው ሕዝብ 24 ሰዓት እየተረባረበ እንደሚገኝና ወደፊትም አጠናክሮ በማስቀጠል የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ይሠራል ነው ያሉት፡፡

የመኖሪያ ቤት ማኅበርን በተመለከተ 2007 ዓ.ም የመጨረሻው ምሪት እንደነበርና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቦታ ስላልተሰጠ የቦታ ፈላጊው ጥያቄ መበራከቱን አመልክተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ለመስጠት ጅምር ሥራዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ 361 ቦታዎች በአዲስ እንዲሸነሸኑ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ቀደም ብሎ ከተሸነሸነው 2 ሺህ 731 ቦታ ጋር 3 ሺህ 92 ሰዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ቦታ በመዘጋጀት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት፡፡

የፋብሪካ እና የሥራ አጥነት ችግርን በተመለከተ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠው ዓባይ ኢንዱስሪያል አክሲዮን ማኅበር በዲዛይን መለወጥ ምክንያት ስለዘገየ የችፑድ ፋብሪካው ፈጥኖ ወደ ሥራ እንዲገባም አሳስበዋል፡፡ የሥራ አጥ ቁጥርና የከተማው የኢኮኖሚ ማመንጨት አቅም አለመመጣጠኑንም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከገጠር ወደ ከተማ የሚገቡ እና ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመልሰው የሚመጡ ሥራ ፈላጊዎች በርካታ ናቸው፡፡ ሥራ መፍጠር የሚያስችል ባለሀብት እና ፋብሪካ ግን የለም፡፡ ወደፊት ለእንደዚህ ዓይነቱ ችግር ራሱን የቻለ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ኅብረተሰቡ ያነሳውን ጥያቄ ወስዶ ለመፍትሔው መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ስለአመራሮች ለተነሳው ጥያቄም ‹‹ከለውጡ ጋር ተያይዞ አመራሩ ለውጡ አልገባውም እየተባለ የተነሳው ጥያቄ በደንብ መታየት አለበት፡፡ ሕዝብና መንግሥት ተረዳድተው ለለውጡ ቀጣይነት መትጋትና ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ እየሰጡ መቀጠል ይገባል›› ነው ያሉት፡፡ 
የመሠረተ ልማት ጥያቄን አስመልክቶ በዞን ደረጃ መፍታት የሚቻል ባለመሆኑ የሚመለከተው የበላይ አካል መፍትሔ እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡ የተጀመረው የመብራት ሰብስቴሽን ተከላ በፍጥነት መሠራት እንዳለበትም ጠይቀዋል፡፡ 
የደብረ ታቦር ከተማን የውኃ ችግር በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም ለአጭር ጊዜ የፍሎራይድ ችግሩን መፍታትና ሌሎች ተጨማሪ የውኃ ጉድጓዶችን በመቆፈር እንደሚያስፈልግ፣ በዘላቂነት ግን የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ነው ዋና አስተዳዳሪው ያሳሰቡት፡፡

የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ደግሞ ‹‹ፖለቲካ የሚዝገው መሪ ከሕዝቡ ጋር ሲራራቅ ነው›› በማለት በየደረጃው ያለ መሪ የሚደርስበት ትችት ከመራራቅ የመጣ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አመራሩ በተቻለው መንገድ የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ቀን ከሌሊት እየሠራ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዮሐንስ የክልሉ ሕዝብ መሪዎቹን መርዳትና ጥፋት ሲኖርም ማረምና መግራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ወቅቱ የሚፈልገው ተጋግዞ የሕዝቡን ጥቅም ማስከበር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የወጣቶች አደረጃጀቶች ተግቶ ሰርቶ ጥቅማቸውን ማስከበር እያለባቸው የፖለቲካ አደረጃጀት እየፈጠሩ እርስ በርሳቸው ድንጋይ የሚወራወሩ ከሆነ ለአማራ ሕዝብ ቀርቶ ለራሳቸው ጥቅም መቆም አያስችላቸውም›› ብለዋል አቶ ዮሐንስ፡፡ ከክልሉ ውጭ ያለው የአማራ ተወላጅ የሚደርስበት የመፈናቀልና የመገፋት ችግር ተቀርፎ ጥቅማቸው እና ሰላማቸው እንዲረጋገጥ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

‹‹ለአማራ ሕዝብ የማይጠቅሙ አስተሳሰቦችን በአፋጣኝ መግታት ያስፈልጋል›› ያሉት አቶ ዮሐንስ የሕገ መንግሥት መሻሻልን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄም ሕጋዊ መስመሩን ጠብቆ እንዲስተካከል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ እና ሌሎችም የፍትሐዊነት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሥራ ለማስጀመር መጀመሪያ ሠላም ማስፈን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንም ኅብረተሰቡ የሰጠው ምክር ጥሩ መሆኑን ገልጸው ከስሜታዊነት ፖለቲካ ነጻ መሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹መሪዎች ብዙ ለሕይወቱ የሚጠቅሙ አማራጮች እያሏቸው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ሕዝባዊ ኃላፊነት የያዙት በሕዝብ ፍላጎት የመጣውን ጥያቄ ለመመለስ በማሰብ ነው›› ብለዋል፡፡ አሁን ያለው አመራር ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩበት ሴራዎች እንዳሉ ያመላክቱት ዶክተር አምባቸው ‹‹ምንም እንኳን የአሁኑ አመራር እንደ እግር እሳት የሚቆጠቁጣቸው ቢኖሩም ወደ ኋላ የሚል አካል የለም፤ ወደፊትም አይኖርም›› ብለዋል፡፡ የአማራን ሕዝብ ክብር ለማስጠበቅ የተጀመረው ጉዞም ስኬታማ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

መንግሥት ሕገ ወጥነትን እንደማይታገስም ነው የተናገሩት፡፡ ኅብረተሰቡ ሕግና ሥርዓትን በማስከበር በኩል ከመንግሥት ጋር መተጋገዝ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ የተነሳው ችግር እና ጥያቄ ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ በተለይ የዳሸን ቢራ ማከፋፈልን የተመለከተው ጥያቄ መፍትሔ እንደሚያገኝም ተናግረዋል፡፡ ‹‹የወቅቱ ፈታኝ ሥራ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ችግር ነው፡፡ ወደ ፊት መንግሥት ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡም መተጋገዝ መቻል አለበት፡፡ የዓለም ባንክ የሚሰጠው በጀት በደብረ ታቦር ከተማ እየታዬ ያለውን የሥራ አጥነት እና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል›› ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

‹‹በክልሉ በተለያዩ አቅጣጫዎች ግፊት እንዲደርስበት ለዘመናት የተሠራው ሥራ እየፈነዳ ችግር እየፈጠረ ነው›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህን ችግሮች ለሕዝቡ ሠላም በተረጋጋ መንፈስ መፍታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.