<> Skip to main content
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከ4ሺህ 233 ሜጋ ዋት ቢደርስም ፍላጎቱን አያሟላም

 

ከኢትዮጵያ ሕዝብ 45 በመቶ ኤሌክትሪከ ኃይል ተጠቃሚ እንደሆነ የዓለም ባንክ ጥናትን በመጥቀስ ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም አስታወቀ፤ሲስተም ላይ ያሉት ደንበኞች ቁጥር ግን 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብቻ ነው፡፡

Image may contain: text

በመሠረተ ልማት አለመሟላት እና በበጀት ችግር ማኅበረሰቡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ አልተቻለም፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ ሀገሪቱ ከፍተኛ ዕምቅ የኃይል ምንጭ ቢኖራትም ኃይል ለማመንጨት የሚያስፈልገው ቴክኖሎጅ ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ ፍላጎቱን ማሳካት እንዳልተቻለ አስታውቋል፡፡

ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ለገሰ የዓለም ባንክ ጥናትን መሠረት አድርገው እንደተናገሩት ከሀገሪቱ ሕዝብ 45 በመቶ በቤተሰብ ደረጃ ቀጥታ እና ቀጥታ ካልሆኑ የኤሌክትሪክ ምንጮች ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው 34 በመቶውን ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቤተሰብ ደረጃ በቀጥታ ከኤሌክትሪክ ምንጮች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከዋናው የኤሌክተሪክ ‹‹ገሪድ›› ጋር የማይገናኙ ምንጮችን እንደ ጀነሬተር፣ ሶላር እና የመሳሰሉ የኃይል ምንጮችን እንደሚጠቀሙ ነው አቶ ጥላሁን የገለጹት፡፡ ይሁን እንጅ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲስተም ላይ ያሉት ደንበኞች ቁጥር 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብቻ እንደሆኑ ነው ዳይሬክተሩ ለአብመድ የገለጹት፡፡
በ2012ዓ.ም መጨረሻ ላይ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሽፋን በከተሞች እና በሦስት ኪሎ ሜትር ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎች ተጠቃሚዎችን 90 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ዕቅዱ በተያዘው በጀት ዓመት 59 ከመቶ ላይ መድረሱን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡ ለኤሌክትሪክ ዝርጋታ የሚያገለግሉ ግብዓቶች አቅርቦት ችግር፣ ለፕሮግራሙ ሥራ እንቅስቃሴ የሚውለው በጀት ከመንግሥት፣ ከዓለማቀፍ አበዳሪ ባንኮች እና ከለጋሽ ድርጅቶች አለመገኘት፣ የመፈፀም አቅም ውስንነት፣ ምቹ የሆነ መንገድ አለመኖር፣ የመልክዓ ምድር አስቸጋሪነት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተከሰተ የመጣው የፀጥታ ችግሮች ዕቅዱን በታለመለት ጊዜ እንዳይከናወን ማድረጋቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደተናገሩት ደግሞ በሀገሪቱ የሚታየውን የኢሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ ተናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የሚታየው የመዘግዬት ችግር ለመፍታትም ከኢፌዴሪ ብረታብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በመረከብ ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ እና በድርጅቱ በንዑስ ተቋራጭነት ሲሰሩ የነበሩ ተቋራጮች እንዲሳተፉ መደረጉን አቶ ሞገስ ነግረውናል፡፡ በ2013 በጀት ዓመትም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ማመንጫዎች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡ በ2015 ዓ.ም ደግሞ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ነው የገለጹት፡፡

አብዛኛው የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ከውኃ የሚገኝ ቢሆንም ከውኃ ውጭ ካሉ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከ400 ሜጋ ዋት በላይ እንደሚገኝ አቶ ሞገስ ነግረውናል፡፡

በ2012 በጀት ዓመት የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ወደ 5 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራም ይገኛል፡፡ ዕቅዱንም ለማሳካት 246 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል የገናሌ ዳዋ ሦስት ፕሮጀክት የግንባታ ሥራው 97 በመቶ ደርሷል፡፡ ከየካቲት 2011 ዓ.ም ጀምሮም ግድቡ ውኃ መያዝ ጀምሯል፤ በ2012 ዓ.ም ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር አቶ ሞገስ ነግረውናል፡፡

ሶማሌ ክልል የሚገኘው አይሻ ሁለት የነፋስ ኃይል ማመንጫ 120 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል ፕሮጀክት ሆኖ እየተገነባ ነው፡፡ የረጲ የደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ እና ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሆነም ነው አቶ ሞገስ የተናገሩት፡፡

ይሁን እንጅ ሀገሪቱ ከፍተኛ ዕምቅ ኃይል ቢኖራትም ኃይል ለማመንጨት የሚያስፈልገው ቴክኖሎጅ ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ ሥራውን ለማሳካት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

ሀገሪቱ ከውኃ፣ ከነፋስ እና ከጅኦተርማል ከሚመነጨው በተጨማሪ በቅርቡ ከደረቅ ቆሻሻ ማመንጨት ትጀምራለች፡፡

Image may contain: text

በዚህ ወቅት 14 የውኃ ኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ ከነፋስ ኃይል እና ከጅኦተርማል 4 ሺህ 233 ሜጋ ዋት፣ በአመት ደግሞ በአማካኝ 16 ሺህ ጌጋ ዋት ማመንጨት አቅም ላይ መደረሱን አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ከውኃ እስከ 50 ሺህ ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚያስችል አቅም እንዳላት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከነፋስ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜጋ ዋት፣ ከጅኦተርማል ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ፣ ከቆሻሻ እና ከፀሐይ ኃይል ማመንጭት የሚያስችል አቅም እንዳላት አቶ ሞገስ ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.