<> Skip to main content
ከኢታኖል ምርት 55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ትርፍ ተገኘ፡፡

ከኢታኖል ምርት 55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማትረፍ መቻሉ ተገለፀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2011ዓ.ም (አብመድ) የፌደራል ማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር በባዮፊውል ልማት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በባሕር ዳር እየመከረ ነው።

Image may contain: one or more people

ከአማራ ክልል እና ከፌደራል የተውጣጡ ባለሙያዎች እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ባዮፊውል ከተለያዩ እጽዋት የሚመረት ነዳጅ ነው። ሀገሪቱ ይህን አማራጭ የኃይል ምንጭ ለማምረት የሚያገለግል እምቅ ጥሬ ዕቃ ቢኖራትም ባላት ውስን ዕውቀት እና የሚያሠራ ሕጋዊ ማዕቀፍ ባለመኖሩ እስካሁን ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያክል ጥቅም ማገኘግ አለመቻሉ ተነግሯል።

በ1999 ዓ.ም ተዘጋጅቶ በነበረው የባዮፊውል ልማት እና ስትራቴጅ መሠረት ግቦችን ከማሳካት አኳያ ዘርፉን ለማበረታታት፣ ለማስተዋወቅ፣ ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር የሚያስችል ሕግ አለመኖር ዋነኛ ክፍተት እንደሆነ ተለይቶ እንደነበር ተጠቅሷል። ይህን ክፍተት ለመሙላት ሚኒስቴሩ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የባዮፊውል ልማት እና አጠቃቀም አዋጅ ረቂቅ በማዘጋጀት ለውይይት እያቀረበ መሆኑ ተገልጿል። ከዚህ ጎን ለጎንም ሀገሪቱንም ለነዳጅ ግዥ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ ከስኳር ተረፈ ምርቶች ኃይል የማምረት ሥራ ሲከናወን መቆየቱ በውይይቱ ተነስቷል።

ምንም እንኳን የባዮፊውል ልማት ተጠንቶ ያላለቀ ቢሆንም እስካሁን ሀገሪቱ ከስኳር ተረፈ ምርት ኢታኖል በማምረት እና ከነዳጅ ጋር በመደባለቅ ለትራንስፖርት፣ ለምግብ ማብሰል እና ሌሎች አገልግሎቶችም እንዲሰጥ በማድረግ 55 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማትረፏ ተገልጿል። ዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ተመጋጋቢ የሆነ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ሂደት እንዲኖር እና ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬን ማግኘት የሚያስችል አቅም ያለው በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ በሕግ እንዲደገፍ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ተብሏል።

የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላም ባዮፊውል ልማት ዘርፉ ሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስታዋጽኦ እንዲያበረክት የውይይቱ ተሳታፊዎች ለረቂቅ አዋጁ አስፈላጊውን ግብዓት በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ መልክት አስተላልፈዋል። ረቂቁ አምሥት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሆኖ በ47 አንቀጾች የተከፈለ ነው።

በፌደራል ደረጃ እስካሁን ሁለት ጊዜ ለውይይት ቀርቧል፤ አብዛኛው ሥራው የሚሠራው በክልል ደረጃ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተመከረበት ይገኛል። ሀገሪቱ በየዓመቱ ከሁለት ነጥብ አምስት እስከ ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለነዳጅ ታወጣለች።

ዘጋቢ- ኃይሉ ማሞ

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.