<> Skip to main content
‹‹ከሁለት ጉድጓዶች በቀን አስከ 100 በርሜል ብቻ ነው የሚወጣዉ፡፡›› የኢፌዴ

‹‹ከሁለት ጉድጓዶች በቀን አስከ 100 በርሜል ብቻ ነው የሚወጣዉ፡፡›› የኢፌዴሪ የማዕድን፣ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 07/2011ዓ.ም (አብመድ) የተፈጥሮ ጋዝ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የኢፌዴሪ የማዕድን፣ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከ350 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የቆዳ ስፋት እንዳለው የሚነገርለት የምሥራቁ የኦጋዴን ሸለቋማ ክፍል እምቅ የተፈጥሮ ማዕድን ሀብት ባለቤት እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በዚህ አካባቢ ያሉ የተፈጥሮ የኃይል አማራጮችን መፈለግ የተጀመረው ከ1970ዎቹ ጀምሮ ነው፡፡ እስካሁን በተደረገው የማዕድን ፍለጋ በተሻለ መልኩ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ መሆኑን ከኢፌዴሪ የማዕድን፣ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ከ8 እስከ 10 ትሪሊን ኪዩቢክ ጫማ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ መገኘቱም ተጠቁሟል፡፡ የማዕድን፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላም እንደተናገሩት በመጀመሪያ ተገኝቶ የነበረው 4 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ነው፤ ይህን ለሀገሪቱ ጥቅም ይሰጥ ዘንድ ጋዙ ከተገኘበት ኦጋዴን አካባቢ እስከ ጅቡቲ የሚያጓጉዝ ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ የተፈጥሮ ጋዙ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሰጥ ከጅቡቲ መንግሥት ጋር ስምምነት ተደርሷል፡፡ የማስተላለፊያ ቱቦ የማምረት ሥራውን ለማከናወን ከቻይና ኩባንያ ጋር ስምምነት ለመፈራረም በሂደት ላይ ነው፤ ዲዛይኑ ወጥቶ ከጸደቀ በኋላ ጨረታው ይፋ ተደርጎ የዝርጋታ ሥራው የሚጀመር መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የተፈጥሮ ጋዝ ማጓጓዣ ቱቦ ዝርጋታውን በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ የታሰበ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ኳንግ በ2021 (እ.አ.አ) ወደ ውጭ የመላክ ሥራው ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

ከዚያው ኦጋዴን አካባቢ እስከ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ያለው ተጨማሪ የተፈጥሮ ጋዝ እንደተገኘ እና እንዴት ባለ መልኩ ልማት ላይ መዋል እንዳለበት ‹ኒው ኤጅ› የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ጥናት እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በኦጋዴን፣ በጋምቤላ እና ከመቀሌ ወደ አፋር ባሉ አንዳንድ ቦታዎች የተለያዩ ኩባንያዎች የተፈጥሮ ጋዝ በመፈለግ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ተገኘ የተባለውም ይሁን በቀጣይ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ እሴት ጨምሮ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ምን ታስቧል በማለት አብመድ ላነሳው ጥያቄም በጥናት እንደተረጋገጠው አሁን ባለው የሀገሪቱ አቅም ውጭ ወስዶ መሸጡ አዋጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በገፀ ምድር ላይ ስለሚታዩ የነዳጅ ምልክቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አማራ ክልልን ጨምሮ በኦጋዴን እና ሌሎች አካባቢዎች በገፀ ምድር ላይ የነዳጅ ምልክቶች መታየታቸው ምልክቱ ከታየበት አካባቢ ነዳጅ መኖሩን አመላካች ነው፤ ነገር ግን የነዳጅ ቅሪት እንደታየ ወደ ሥራ ለመግባት አስቸጋሪ ነው፡፡ በጥናት የተደገፈ ካልሆነ ተጨማሪ ወጭ ሊያስወጣ የሚችል ሊሆን ይችላል፡፡ ቅሪቱ ከሚታይበት አካባቢ ነዳጅ በጣም ርቆ የሚገኝበት አጋጣሚ ብዙ ስለሆነ ክምችቱን እና የኢኮኖሚ አዋጭነቱን በማጥናት የምንመልሰው ይሆናል›› ነው ያሉት፡፡
በኦጋዴን አካባቢ ከዚህ ቀደም ‹‹ነዳጅ ተገኘ›› ተብሎ ለሕዝብ ተበስሮ የነበረውንና ቁፋሮ እየተካሄደ ያለውን ቦታም እንደማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ነዳጅ ተገኘ ተብሎ በሙከራ ምርት ደረጃ ቁፋሮ እየተካሄደበት በሚገኘው አካባቢ ከሁለት ጉድጓዶች በቀን አስከ 100 በርሜል ብቻ ነው የሚወጣዉ፡፡ ይህ ደግሞ አጥጋቢ አይደለም›› ነው ያሉት፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የነዳጅ ቅሪት በሚታይባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥናት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓባይ በርሃ፣ በስምጥ ሸለቆ፣ ኦጋዴን፣ ጋምቤላ፣ መተማ እና ከመቀሌ እስከ አፋር ክልል ያሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች እምቅ የነዳጅ ሀብት ይገኝባቸዋል ተብለው ከተለዩ ስድስት አካባቢዎች መካከል ናቸው፡፡

ዘጋቢ-ሀይሉ ማሞ

ምስል፡- ከድረገጽ

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.