<> Skip to main content
የደሴ የዘር ብዜት ማዕከል ሰኔ 04 ሊመረቅ ነው፡፡

በደሴ ከተማ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የዘር ብዜት ማዕከል ግንባታ ተጠናቀቀ፡፡

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 1/2011ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የክልሉን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን የሚያስችል የዘር ብዜት (የቲሹ ካልቸር) ማዕከል በደሴ ከተማ አስተዳደር አስገንብቶ ለሥራ ዝግጁ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የምርምር ማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አበበ ግርማ እንደተናገሩት ማዕከሉ ዘራቸው ውስን የሆኑ፣ ጥራት ያላቸው እና ገበያ ተኮር የሆኑ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡

 

ማዕከሉ በዓመት ሁለት ጊዜ ምርት የሚሰጡ አትክልት እና ፍራፍሬዎች ላይ እንደሚሠራም ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል፡፡ ለቆላ እና ደጋ የአየር ንብረት ተስማሚ እንዲሆን የሚያደርግ የዕፅዋት ማበልፀጊያ ቴክኖሎጅ ማዕከሉ እንዳለውም ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የተናግሩት፡፡

ዶክተር አበበ እንደገለፁት ማዕከሉ በክልሉ ከበሽታ ነጻ የሆኑ ችግኞችን በበቂ ቁጥርና ጥራት ያመርታል፤ ችግኞች ከአርሶ አደሩ ከደረሱ በኋላም በሽታን መቋቋም እንዲችሉ ይሠራል፡፡ በዓመት 30 ሚሊዮን ችግኝ የማባዛት አቅምም እንዳለውና በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ግዙፍ የዕፅዋት ማባዣ እንሆነም ታውቋል፡፡

 

የምርምር ማዕከሉ የፊታችን ሰኔ 04 ቀን 2011ዓ.ም እንደሚመረቅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

 

 

 

 

Image