<> Skip to main content
ለሌሎች ተማሪዎች ሊፈተኑ ነበር የተባሉ ግለሰቦች ተጋለጡ፡፡

ለሌሎች ተማሪዎች ሊፈተኑ ነበር የተባሉ 11 ግለሰቦች መጋለጣቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ሁለተኛ ቀኑን ይዟል፡፡ ስለፈተናው ሂደት የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን ጠይቀናል፡፡

Image may contain: one or more people

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሚዩኒኬሽን እና ሚዲያ ልማት ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሰኢድ አህመድ በተለይም ለአብመድ እንደገለጹት ተፈታኞችን ተክተው ሊፈተኑ ከነበሩት 11 ግለሰቦች መካከል ስድስቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው፡፡ አምስቱ ደግሞ በቦታው ባለመገኘታቸው ምክንያት በቁጥጥር ስር ባይውሉም ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ የመፈተኛ ጣቢያዎች 971 ስልኮችን ይዘው ሊገቡ ሲሉ በተደረገ ፍተሻ ማስቀረት ተችሏል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በሁሉም የክልሉ የመፈተኛ ጣቢያዎች ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አልተፈጠረም ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፡፡ ፈተናው ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቅም የፀጥታ አካላት ከፈታኝ መምህራን እና ከፈተና ተቆጣጣሪዎች ጋር በቅርበት እየሠሩ እንደሆነ ነው ያስታወቁት፡፡

ተማሪዎች፣ የፈተና ተቆጣጣሪዎች፣ ወላጆች እና ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር እያደረጉት ላለው ትብብርም ምክትል ኮሚሽነሩ አመስግነዋል፡፡

ተማሪዎች የፈተና ህጉ በሚፈቅደው መሠረት እንዲፈተኑ፣ ወላጆችም ልጆቻቸው በሥርዓት እንዲፈተኑ መምከርና መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

 ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

Image