<> Skip to main content
ባለፉት ስድስት ወራት በዓለም ላይ 38 ጋዜጠኞች ለኅልፈት ተዳርገዋል ተባለ፡፡

 

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 28/2011 ዓ.ም (አብመድ) ሰሜን አሜሪካ ከፍተኛ የጋዜጠኞች ጥቃት የሚስተዋልበት አህጉር እየሆነ መጥቷልም ተብሏል፡፡

No photo description available.

ከአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር መጀመሪያ ጥር 2019 ጀምሮ እስከ ሰኔ 2019 መጨረሻ ድረስ ባሉት ስድስት ወራት በዓለም ላይ 38 ጋዜጠኞች መገደላቸውን መቀመጫውን ጀኔቫ ላይ ያደረገው ፕረስ ኢምብለም ካምፔይን (ፒኢሲ) አስታውቋል፡፡

የጋዜጠኞች ጥቃት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 42 በመቶ መቀነሱ መልካም አጋጣሚ ነው ብሏል ፕረስ ኢምብለም ካምፔይን፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ የዘጠኝ ጋዜጠኞች ህይወት ያለፈው በሜክሲኮ እና ስድስቱ የሞቱት ደግሞ በአፍጋኒስታን ብቻ መሆኑ ጉዳዩን አስደንጋጭ አድርጎታል ተብሏል፡፡
በአፍጋኒስታን ‹‹የአሸባሪ ቡድን›› አባላት እና በሜክሲኮ የሚገኙ የወንጀለኛ ቡድኖች ባለፉት ስድስት ወራት ለተፈፀመው የጋዜጠኞች ጥቃት ቀዳሚውን ኃላፊነት ይወስዳሉም ነው የተባለው፡፡

የፕረስ ኢምብለም ካምፔይን ዋና ፀኃፊ ብሌዝ ሌምፐን እንዳሉትም ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ በየሀገራቱ ያሉትን የሚዲያ ተቋማት ለመጠበቅ፣ ከጥቃት ለመከላከል እና ነፃነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስልቶችን በመቀየስ መስራት ይኖርበታል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ የሚስተዋለው የጋዜጠኞች ጥቃት ቢቀንስም ሰሜን አሜሪካ ከፍተኛ የጋዜጠኞች ጥቃት የሚስተዋልበት አህጉር እየሆነ መጥቷልም ተብሏል፡፡
ፕረስ ኢምብለም ካምፔይን ባለፈው ዓመት በዓለም ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ጥቃት በግማሽ ለመቀነስ እንዲቻል ከመንግስታት፣ ከድርጀቶች እና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በጋራ ለመስራት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡- ሽንዋ

በታዘብ አራጋው

Image