<> Skip to main content
ለሦስት ዓመታት የታመመው ሽምብራ መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡

ለሦስት ዓመታት የታመመው ሽምብራ መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 4/2011 ዓ.ም (አብመድ) በተያዘው የመኸር ወቅት በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ሽምብራ አብቃይ አካባቢዎች 16 ሺህ ሄክታር መሬት ሽምብራ ለመዝራት ታቅዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 5 ሺህ 180 ሄክታሩ የሚሆነው መሬት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የሚገኝ ነው፡፡ በኩታ ገጠም ሽምብራ ለመዝራት ከታቀዱ ሦስት ወረዳዎች ምንጃር ሸንኮራ አንዱ ቢሆንም የሽምብራ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ እንዳይዘራ ተወስኗል፡፡

በወረዳው ያለውን ከፍተኛ ሽፋን እና ምርታማነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጥናት አድጎ ‹የአረርቲ ሽምብራ› የተሻለ ዝርያ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ‹የአረርቲ ሽምብራ› የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አርሶ አደሮችም ትኩረት ሰጥተው በመዝራት ከፍተኛ የሽምብራ ምርት ሲያመርቱ ቆይተዋል፡፡ ከሦስት ዓመት ወዲህ ግን በሰብሉ ላይ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ ምርታማነቱም ሆነ የሽፋን መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል፡፡ የወረዳው አርሶ አደሮችም መዝራት በማቆማቸው ከሽምብራ ምርት ያገኙት የነበረውን ጥቅም አጥተዋል፡፡

Image may contain: plant, tree, nature and outdoor

ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ‹ስር አበስብስ› የተባለው ይህ በሽታ ሰብሉ ከበቀለ በኋላ ስሩን በማበስበስ የሽምብራ ምርትን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል፡፡ የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤትም የበሽታውን አሳሳቢነት ለደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር፣ ለደብረ ዘይት እርሻ ምርምር፣ ለኮምቦልቻ ዕፅዋት ኳራንታይን እና ለክልሉ ግብርና ቢሮ አሳውቋል፡፡ እነዚህ ተቋማት አርሶ አደሮች የሽምብራ ሰብልን ደረቃማ ቦታ እንዲዘሩ፣ እርጥበታማ ቦታዎችን እንዲያጠነፍፉ እና ዘግይተው እንዲዘሩ ምክረ ሐሳብ ከማቅረብ የዘለለ ሳይንሳዊ መፍትሔ አላገኙለትም፡፡ የምንጃር ሸንኮራ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እጅጉ እንደተናገሩት አርሶ አደሮች ከተቋማቱ የተሰጡትን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ቢያደርጉም በሽታውን ግን ማስቀረት አልተቻለም፡፡

Image may contain: plant, nature and outdoor

አቶ ተስፋዬ ለአብመድ እንደገለጹት በሽታው በውኃ፣ በነፋስ እና በተለያዩ አጋጣሚዎችና ምክንያቶች ከቦታ ወደ ቦታ የሚዛመት በመሆኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በኩታ-ገጠም ለመዝራት ከታቀዱት ዋና ዋና ሰብሎች መካከል ሽምብራ አልተካተተም፡፡ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ እንደ ምሳሌ ይጠቀስ እንጂ በዞኑ ሽምብራ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በሽታው መከሰቱን ከዞኑ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በመረጃውም መሠረት ስር አበስብስ ከሚባለው በሽታ በተጨማሪ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ‹ቫይራል ዲዚዝ› የሽምብራ በሽታም ተከስቷል፡፡

የደብረ-ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል ለበሽታው መፍትሔ በመፈለግ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ዐብይ ለገሰ እንዳስታወቁት የማዕከሉ ተመራማሪዎች ከሌላ የምርምር ተቋማት ጋር ከሽምብራ አብቃይ አካባቢዎች ናሙና ወስደው የበሽታውን ምንነት እና መከላከያ ዘዴዎች ለመለየት ተሞክሯል፡፡ በሽምብራ ሰብሉ ላይ የተከሰተው በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት በመሆኑ ለመከላከል መደረግ ያለበት የበሽታውን አምጭ ተህዋስያን በመቆጣጠር ባለበት ማቆየት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹እፊት›› የተባለውን ነፍሳት ጨምሮ ከሰብሉ ጋር ንክኪ ያላቸውን ተባዮች መቆጣጠር ከተቻለ በሽታው እንዳይዛመት መድረግ እንደሚቻልም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይህንን ዘዴ ለአርሶ አደሮች እና ለግብርና ባለሙያዎች መረጃ እንዲደርስ አድርገናል›› ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ የምርምር ማዕከሉም ቀጣይ ይህንን ተህዋሲያን የሚቆጣጠር መድኃኒት እና በሽታውን ሊቋቋም የሚችል ዝርያ ለመለየት እንደሚሠራ ነው ያስታወቁት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Image