<> Skip to main content
በአማራ ክልል ቡናን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተመረተ አለመሆኑ ተገለፀ፡፡

በአማራ ክልል የቡናን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመረዳት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተመረተ አለመሆኑ ተገለፀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 4/2011 ዓ.ም (አብመድ) ለቤት ፍጆታ ብቻ ከማምረት ውጭ የቡናን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በአግባቡ በመረዳት እየተመረተ አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አውግቸው ተሾመ እንደተናሩት በኢትዮጵያ ለቡና ምርት በከፍተኛ ደረጃ ምቹ የሚሆን አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት መኖሩ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ በከፍተኛ እና መካከለኛ ደረጃ በጥቅሉ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለቡና ምቹ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በተጨባጭ በቡና የተሸፈነው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ ነው፡፡ 

Image may contain: plant
በአማራ ክልል ደግሞ 361 ሺህ ሄክታር በከፍተኛ ደረጃ እንደዚሁም ደግሞ በሚሊዮን ሄክታር የሚለካ መሬት በመካከለኛ ደረጃ ለቡና ተስማሚ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል፡፡

በክልሉ ግብርና ቢሮ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ላቃቸው እምሩ ለአብመድ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ለቡና ባለው ተስማሚነት አማራ ክልል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይ በምሥራቅ አማራ የተሻለ ጥራት ያለው የቡና ምርት እንደሚገኝ በጥናት ቢረጋገጥም ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመሩት ግን ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም፣ አዊ፣ ደቡብ ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ብቻ ናቸው፡፡

Image may contain: outdoor

ለቡና አስቦ እና ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ ባለመሆኑ ክልሉ ባለው የመልማት አቅም ልክ ተጠቃሚ ሳይሆን ለረጅም ዘመናት ቆይቷል፡፡ አርሶ አደሮችም ለቤት ፍጆታቸው ከማምረት ውጭ የቡናን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በአግባቡ በመረዳት እምብዛም እንዳልሠሩበት ነው የተገለጸው፡፡

ዘግይቶም ቢሆን የክልሉ መንግሥት ቡና የሚያስገኘውን የውጪ ምንዛሪ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በትኩረት እየሠራ እንደሆነ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በ2010 ዓ.ም በ2 ሺህ 645 ሄክታር መሬት ላይ 140 ሺህ 400 በላይ ኩንታል ቡና ማምረት ተችሏል፡፡ በዘርፉ 24 ማኅበራት በአንድ ዩኒየን ስር ሆነው በፍኖተ ሠላም ከተማ ዘመናዊ መጋዘን እየገነቡ ነው፤ ዘመናዊ የቡና መፈልፈያ ማሽንም አስገብተዋል፡፡ ‹‹የቡና ምርትን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግና የኅብረተሰቡን ንቃተ ኅሊና ለማሳደግ ቡና ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ተቋም ያስፈልጋል›› ብለዋል በለሙያዎቹ፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮም ይህ ተቋም እንዲቋቋም ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ባለው የዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የዓለም የቡና ምርት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ኢትዮጵያ ያላትን የቡና ምርት በማስቀጠል ተጨማሪም ማስፋት የምትችልበት ትልቅ ዕድል እንዳላት ነው የተገለጸው፡፡ አብዛኞቹ ቡና አምራች ሀገራት የቡና ምርታቸው ቅናሽ በሚያሳይበት ጊዜ በኢትዮጵያ ምቹ ተብሎ ከተለዬው በላይ መሬት ሊኖር እንደሚችል እና በአማራ ክልልም ጭማሪ ሊኖረው እንደሚችል ተመላክቷል፡፡

እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች ማብራሪያ የቡና ምርትን ለማሳደግ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የማረም፣ መኮትኮት፣ ያረጀውን ዛፍ የመጎንደል እና ምርታማነቱ ቅናሽ የታዬበትን በተሻሻለ ዝርያ የመተካት ሥራ ያስፈልጋል፡፡ የቡና ተክል ረጅም ጊዜ ወስዶ ጥቅም የሚሰጥ በመሆኑ የአፈር ጥበቃ እና እርጥበት እቀባ ላይ በትኩረት መሥራት ይጠይቃል፡፡

የተለያዩ የቅመማ ቅመሞችን፣ ፍራፍሬዎችን እና የጓሮ አትክልቶችን በጋራ የማልማት ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግና በቀጣይ ምርምርና ኤክስቴንሽን ሥራው እንዲጠናከር እና ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን በክልል ደረጃ መዋቅር ተፈጥሮለት እና የሰው ኃይል ተዘጋጅቶለት እንደሚሠራ ተነግሯል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ምስል፡- ከድረ ገጽ

Image