<> Skip to main content
ከተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 80 በመቶው በአሽከርካሪዎች ጥፋት መሆኑ ተነገረ፡፡

ከተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች 80 በመቶው በአሽከርካሪዎች ጥፋት መሆኑ ተነገረ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 4/2011 ዓ.ም (አብመድ) የትራፊክ አደጋ የሚያደርሰውን ጉዳት መከላከል የሁሉም ዜጋ ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የትራፊክ አደጋ በሰብዓዊ ሀብት፣ በኢኮኖሚ እና በዜጎች ሥነ ልቦና ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ከአማራ ክልል መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ባለፉት 11 ወራት ብቻ በክልሉ 2 ሺህ 748 አደጋዎች ደርሰዋል፤ 846 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ1 ሺህ 870 በላይ ሰዎች ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አደጋው በሀገርም ሆነ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ አሳድሮት ያለፈው ተፅዕኖም ቀላል አይደልም፡፡ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም ወድሟል፡፡

Image may contain: one or more people, car and outdoor

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳው ማንኛውም ገዳይ በሽታ ከመቶ ሰዎች የአንዱን ሕይወት መንጠቅ ከቻለ ወረርሽኝ ተብሎ ይፈረጃል፡፡ የትራፊክ አደጋም ከወረርሽኝ ባልተናነሰ ሕጻናት እና ታዳጊዎችን፣ ጎልማሶችና አረጋውያንን ዘር፣ ቀለም ሳይለይ እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ በአደጋው ምክንያት በርካቶች ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው እንደወጡ ቀርተዋል፡፡ እግረኞች፣ አሽከርካሪዎች፣ የመንገዶች ጥራት እና የተሸከርካሪዎች የአገልግሎት ሁኔታ የአደጋው መንስኤዎች ተደረገው ቢቆጠሩም በአሽከርካሪዎች የጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት የተከሰቱ አደጋዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ያኘነው መረጃ ያመልከታል፡፡

Image may contain: car, sky, outdoor and nature

ባለፉት 11 ወራት ከደረሰው አደጋ ውስጥ 1 ሺህ 613 ያክሉ ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር፣ ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠት፣ ለተሽከርካሪ ቅድሚያ ባለመስጠት እና ርቀትን ጠብቆ ባለማሽከርከር የተፈጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህም በዓመቱ ከተከሰቱት አጠቃላይ አደጋዎች ውስጥ 80 በመቶ ያክሉን ይይዛሉ፡፡ ስማቸው እንዳይገለፅ በመጠቆም ለአብመድ አስተያዬታቸውን የሰጡ አሽከርካሪዎች እና ዕጩ ሰልጣኞች እየደረሰ ላለው ጉዳት የአሽከርካሪዎች የብቃት ማነስ በዋነኛነት የድርጊቱ መንስኤ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

በባሕር ዳር ከተማ በሚገኙ የተለያዩ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት መንጃ ፈቃድ ለማግኘት እየሰለጠኑ ያሉ ሰልጣኞች እንደነገሩን ችግሩ የሚሰጠው የስልጠና ጊዜ ማነስ እና መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን ነው፡፡
ይህም ሆኖ በአብዛኞቹ ተቋማት የሚሰጠው ስልጠና መርሀ ግብሩን ለማሟላት እንጅ የሰልጣኞችን ንድፈ ሐሳባዊ እና ተግባራዊ ክህሎት ለመገንባት እንዳልሆነ መታዘባቸውን ገልፀውልናል፡፡ በተያዘው ጊዜ ልክ ስልጠናውን አለመስጠት፣ ለስልጠናው አስፈላጊ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን እና ሰርቶ ማሳያ ክፍሎች አለማሟላት የሚታዩ ክፍተቶች እንደሆኑም አብራርተዋል፡፡ ወጭ ለመቀነስ ሙሉ የስልጠና ጊዜውን አለመጠቀም እና ከክህሎቱ ይልቅ ወረቀቱን ለማግኘት የመጓጓት ፍላጎት በአብዛኞቹ ሰልጣኞች እንደሚታዩም አስረድተዋል፡፡

በአሽከርካሪዎች ችግር የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች እያሳሰባቸው መሆኑን እና እልባት ሊያገኝ እንደሚገባ የጠቆሙት ‹‹ስማችን እንዳይገለፅ›› ያሉ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የአሽከርካሪ ተቋማት ባለንብረቶች ናቸው፡፡ ባለንብረቶቹ ለስልጠናው ጥራት መጓደል እራሳቸውን ተወቃሽ አድርገዋል፡፡ ስልጠናውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተከታትሎ አለመስጠት፣ በቂ እና ምቹ የሆነ የስልጠና ቦታዎችን ሳያመቻቹ ስልጠና መስጠት፣ በአሮጌ እና ውስን ተሽከርካሪዎች ማሰልጠን በተቋማቱ ከሚስተዋሉ የአሠራር ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑና መታረም እንዳለበት ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

የመጨረሻውን የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጠው የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ለብቃት መጓደሉ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ባለንብረቶቹ አስረድተዋል፡፡ እነርሱ እንዳሉት ቢሮው ብቃት የሌላቸው ሰልጣኞች ሲያጋጥሙት የብቃት ፈተናውን አለማሳፍ ይችል ነበር፤ በብዛት ግን እየሆነ አይደለም፡፡ ‹‹ብቃት የላቸውም›› የሚባሉት አሽከርካሪዎች በምዘና አልፈው ማረጋገጫ የተሰጣቸው ናቸው፡፡

የአማራ ክልል መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ጌታቸው ገዛኸኝ በበኩላቸው ከአሽከርካሪዎች ብቃት ጋር ተያይዘው የተነሱ ችግሮች ተገቢ መሆናቸውን እና ቢሮው ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ለማስተካከል እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

 

እንደ እርሳቸው ገለፃ የአሰልጣኝ ተቋማትን አቅም ለማጠናከር እና የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሠራ ነው፡፡ የተሰጣቸውን ሙያዊ ኃላፊነት በመተው ለሰልጣኞች ብቃት መጓደል ምክንያት ናቸው ባላቸው አካላት ላይም ቢሮው ክስ መስርቷል፡፡

የቢሮው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አዳነ ደግሞ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ኃላፊነት በተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት መደበኛ አሠራር መከላከል እና መቀነስ አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡

የሚድያ አካላት፣ የፍትሕ ተቋማት እና የሚመለከታቸው ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡ በቅርቡም ሁሉንም አካላት ያሳተፈ የጋራ የሚዲያ ፎረም በእንጅባራ ከተማ ተቋቁሟል፡፡

በአማራ ክልል ብቻ 89 ሺህ ተሸከርካሪዎች አሉ፡፡ እነዚህንና በሌሎች ክልሎችየተመዘገቡ ተሽከርካሪዎችን የሚቆጣጠሩ የመንገድ ደኅንነት ባለሙያዎች ግን 240 ብቻ ናቸው፡፡ ይህም አንድ ባለሙያ በአማካይ ከ370 በላይ ተሽከርካሪን ይቆጣጠራል እንደማለት ነው፡፡

በአማራ ክልል በየቀኑ ሦስት፣ በየወሩ 90 ሰዎች በአማካይ ሕይወታቸውን በመኪና አደጋ ያጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ በቀን 14 ሰዎች፣ በዓመት 5 ሺህ 118 ሰዎች በአደጋው እንደሚሞቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

ፎቶ፡- ከድረገጽ

Image