<> የለውጥ ኃይሉን በመደገፍ ከሕዝብ ጋር ለውጡን ዳር ማድረስ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ | Amhara Mass Media Agency Skip to main content
የለውጥ ኃይሉን በመደገፍ ከሕዝብ ጋር ለውጡን ዳር ማድረስ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

 

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 8/2011 ዓ.ም (አብመድ) የትህነግ (ህወኃት) መግለጫ በአማራ ክልል ባለስልጣናት ላይ የደረሰውን ጥቃት እንደ መልካም አጋጣሚ የመጠቀም ሁኔታ የታዬበትና ከሕግ አግባብ ውጭ በድርጊቱ ላይ ድምዳሜ የደረሰበት እንደሆነ የሕግና የአመራር ባለሙያና የአብን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አዲሱ ሐረገወይን ተናግረዋል፡፡

አቶ አዲሱ እንደተናገሩት ትህነግ በሕግ አግባብ የተያዘን ጉዳይ አስቀድሞ አዴፓን ጥፋተኛ አድርጎ በመበየን ይቅርታ እንዲጠይቅ በመግለጫው ማሳሰቡ የትህነግን ወደ መሀል ሀገር ፖለቲካ ለመመለስ የተቀመረ ወቅታዊ ሴራ አመላካች ነው፡፡ ‹‹ትህነግ አዴፓን በማጥቃት እንደ አብን ያሉ የክልሉን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖችንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ለማፈን የፈጠራት ሴራ ነች፤ አዴፓን አንገት ለማስደፋትና እኛን ለማሳደድ የተፈጠረ ስልት ነው፤ ነገር ግን በአዴፓ መግለጫ ሴራው ከሽፏል›› ብለዋል፡፡

‹‹የባለስልጣናቱ ግድያ ሁኔታ ገና በመጣራት ላይ እያለ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ተገቢ አልነበረም፤ ከዚያ ውጭ ለትህነግ የተሰጠው ምላሽ ግን ተገቢ ነው›› ብለዋል አቶ አዲሱ፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰት በሕግ የሚጠየቁ ግለሰቦችን ለበርካታ ወራት ደብቆ የሚገኝ ድርጅት አንድ ወር ላልሞላው ድርጊት ፍትሕ መጠየቁ ቅቡልነት እንደሌለውም ነው ያመለከቱት፡፡ የሁለቱ እህት ፓርቲዎች ወደ ንትርክ መግባት ኢህአዴግን ወደ ችግር እንያዳስገባው ያላቸውን ስጋትም ተናግረዋል፡፡

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ከአዴፓ ጋር በመሆን የአማራ ሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መጠናከር እንደሚገባም አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያና አጠቃላይ የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካን በመተንተን የሚታወቁት ፖለቲከኛ አቶ ወንድወሰን ተሾመ ደግሞ ‹‹የህወኃት አዴፓን ይቅርታ ይጠይቅ መግለጫ ድፍረት የተሞላትና ሥነ-ምግባራዊ ያልሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ለውጥ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር ዋጋ የከፈለ ፓርቲ ውድ ልጆቹን አጥቶ በሐዘን ላይ ተቀምጦ እያለ ይቅርታ ጠይቅ መባሉ ያበሳጫል፤ ኃላፊነት የጎደለውም ነው›› ብለዋል፡፡

እውነታው ከታዬ ይቅርታ መጠየቅ ያለበት ትህነግ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ወንድወሰን ተሾመ ለ27 ዓመታት በወንጀል ሥራ የቆዩ ተጠርጣሪዎችን አቅፎ የያዘ ድርጅት ‹‹ይቅርታ ጠይቁኝ›› ሲል አግራሞትን እንደሚያጭርም ነው የገለጹት፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው በቅርቡ በመሆኑና ውስብስብ በመሆኑ ድምዳሜ ላይ ደርሶ አዴፓን ጥፋተኛ ማለት የሚያስችል ሁኔታ ገና አለመኖሩን ያስታወቁት አቶ ወንድወሰን ‹‹ማንም ድምዳሜ ላይ መድረስ አይችልም፤ መረጃው ጠርቶ በሕግ መወሰን አለበት›› ብለዋል፡፡

አዴፓ ያወጣውን መግለጫ በተመለከተም ‹‹የተፈጸመበት ትንኮሳ በዝምታ መታለፍ ስላልነበረበት መመለሱ የግድ ነበር፤ ያወጣው መግለጫም ጨዋነት የታዬበትና ኃላፊነት የተሞላበት፤ የትግራይን ሕዝብና ህወኃትን የለዬ ነበር›› ብለዋል፡፡

በኢህአዴግ ውስጥ ሦስት ዓይነት ኃይል መኖሩን እንደታዘቡም አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ላይ ኢህአዴግ በውስጡ የለውጥ ኃይል፣ ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልግና ወደ አሸናፊው ሊጠጋ የሚፈልግ ኃይል አለ፡፡ በመጨረሻ የለውጥ ኃይሉ እንደሚያሸንፍ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አዴፓ እንደ ለውጥ መሪ ደግሞ ለውጡን ለመቀልበስ የሚጎትቱትን የማስታመም ኃላፊነት የለበትም፡፡ ለውጡን ለማቀጠል ፍላጎት የሌላቸው የኢህአዴግ አባላትንም ቢሆን እየጣሉ ማለፍና ከሕዝብ ጋር ለውጡን ዳር ማድረስ ይገባል›› ነው ያሉት፡፡

ለውጡ በለዘብተኛ ሁኔታ ከሚቀጥልና የለውጥ መሪዎችን ከሚያሳጣ ቆፍጠን ብሎ በአነስተኛ መሰዋዕትነት ዳር መድረስ እንዳበትም ነው አቶ ወንድወሰን ያሳሰቡት፡፡ አዴፓ ክልላዊና ሀገራዊ ኃላፊነት ያለበት የለውጥ ኃይል ያለው ፓርቲ በመሆኑ ሁሉም የለውጥ ኃይል በጋራ ከጎኑ መቆም እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.