<> Skip to main content
የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪዎች ስጋት ሆኗል፡፡

‹‹የቡሬ የመብራት ኃይል አቅርቦት በፍጥነት አለመሟላቱ ለኢንዱስትሪዎች ስጋት ሆኗል፡፡›› የቡሬ ከተማ አስተዳደር

‹‹በገንዘብ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመው ቦርድ የሚያዘጋጀው የሕግ ማሻሻያ መጓተት ለኃይል አቅርቦቱ መዘግየት ምክንያት ሆኗል፡፡›› የኢትጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

Image may contain: sky, bridge, tree and outdoor

‹‹ሥራው ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ መዘግየት ተፈጥሯል፡፡›› የገንዘብ ሚኒስቴር

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 9/2011 ዓ.ም (አብመድ) በቡሬ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ቢኖርም የኃይል አቅርቦት ችግር መኖሩ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት አጥናፉ ለአብመድ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ መንግሥት የሚገነባውን የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ ከ23 በላይ የተለያዩ ኢንዱስተሪዎች በግንባታ ሂደት ላይ አሉ፡፡ ተጨማሪ ባለሀብቶችን ለመሳብ ከተማ አስተዳደሩ የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም የኃይል አቅርቦት ችግሩ ግን እንቅፋት ሆኖበታል፡፡

እንደ አቶ ጌትነት ገለጻ በአቶ በላይነህ ክንዴ አማካይነት እየተገነባ የሚገኘው የዘይት ፋብሪካ ኢትዮጵያ ለፓልም ዘይት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በግማሽ ይቀንሳል የተባለለትን ግዙፍ የዘይት ፋብሪካ ጨምሮ ሌሎች ፋብሪካዎችም ወደ ምርት ለመግባት ግንባታቸው ተጠናቅቆ በማሽን ተከላ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በከተማው ያለው የኃይል አቅርቦት በአነስተኛ እና ጥቃቅን የተደራጁ ወጣቶችን እንኳን ማስተናገድ ያልቻለ በመሆኑ ወደ ሥራ ለመግባት ችግር እንደሆነባቸው ነው ያስታወቁት፡፡
የአማራ ከልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሴ አሰሜ ደግሞ የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ የሕንጻ ግንባታ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ግንባታቸው እየተከናወነ ከሚገኙት ፋብሪካዎች መካከልም አብዛኞቹ በ2012 ዓ.ም መጀመሪያ ግንባታቸው ተጠቅቆ ለሥራ ዝግጁ እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ የመብራት ኃይል አቅርቦት ችግሩ ከወዲሁ መፈታት ካልቻለ እንደሚቸገሩ ነው ያስታወቁት፡፡

አቶ ደሴ የመብራት ኃይል አቅርቦት ችግር መፍትሔ እንዲሰጠው የክልሉ መንግሥት በአካል እና በጽሑፍ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን ነው ያስታወቁት፡፡ ከመጋቢት 2011ዓ.ም ጀምሮም ለስብስቴሽን ግንባታ የሚሆን መሬት ከሦስተኛ ወገን ነጻ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራውን በፍጥነት ማከናወን አልቻለም፡፡ የመብራት መቆራረጥ ችግር የቡሬ ከተማ የረጅም ጊዜ ችግር ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው ‹‹የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ወደ ሥራ እንዲገባ ከተፈለገ የመብራት ኃይል አቅርቦት በፍጥነት መሟላት አለበት›› ብለዋል፡፡

Image may contain: sky, outdoor and nature

የኢትጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለአብመድ እንተደናገሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል መሠረተ ልማት በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሟላ ባለመሆኑ የሚገነቡት በመንግሥት እና በግል የልማት ድርጅቶች አጋርነት ነው፡፡ የመንግሥት እና የግል አጋርነትን በቅርበት የሚከታተል በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ቦርድ እንደተቋቋመም ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የሥራ ድርሻ የአዋጭነት ጥናት ማዘጋጀት፣ የቅድመ ዲዛይን እና ዝርዝር የዲዛይን ሥራ ማዘጋጀት መሆኑንም አቶ ሞገስ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ተቋሙ የአዋጭነት ጥናት አዘጋጅቶና የቅድመ ዲዛይን ሥራውን አጠናቅቆ ዝርዝር የዲዛይን ሥራ በማዘጋጀት ላይ ነው›› ያሉት አቶ ሞገስ ቦርዱ የሚያዘጋጀው የሕግ ማሻሻያ መጓተት ለኃይል አቅርቦቱ መዘግዬት ምክንያት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ቦርዱ ቀሪ ሥራዎችን አጠናቅቆና ገንዘብ አዘጋጅቶ በፍጥነት ውል የሚፈጽም ከሆነ ሰብስቴሽኑ በአጭር ጊዜ ይሠራል ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ ሥራው ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ መዘግዬት መፈጠሩን ነው የገለጸው፡፡ በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሀጂ ኢብሳ የግልና የመንግሥት አጋርነት ለሀገሪቱ አዲስ በመሆኑ፣ የሕዝብ ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱና በጨረታ ላይ የሚሳተፉ የግል ድርጅቶችንም በጥንቃቄ ማሳተፍ ስለሚያስፈል መዘግዬት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ በሂደት ላይ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ የአራት ፕሮጀክቶች ጨረታ አሸናፊ ዛሬ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፤ ከአራቱ ውስጥ ግን ቡሬ ስለመካተት አለመካተቱ አልገለጹም፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ፎቶ፡- ከፋይል

Image