<> Skip to main content
በሻደይ የወንዶች ሚና እና የፍቅር ክዋኔዎች!

…በሻደይ ወቅቶች የተጠነሰሰ ፍቅር…የሽምግልና ስርዓቱ እንዲቀጥል ሆኖ ወደ ትዳር ይሻገራል፡፡

Image may contain: 8 people, people standing and outdoor

የሻደይ ጨዋታ ተምሳሌቱ ሀይማኖታዊ ነው፡፡ ሻደይ ለሴቶች የነጻነት ማብሰሪያም ነው፤ በነጻነት ከአቻዎቻቸው ጋር ይጫወታሉና፡፡ ለመሆኑ በሻደይ ጨዋታ የወንዶች ሚና ምንድን ነው? የዋግ ኽምራ ወጣት ወንዶች አብዛኛውን ጊዜ ከነሀሴ መጀመሪያ ቀናት ጀምሮ ክምክም ጎፈሪያቸውን የሚያስውብ ልዩ መዓዛ ያለው ቅባት ይቀባሉ፡፡ ቅባቱ ተፈጥሯዊ ነው፤ በተፈጥሯዊ ውበት ላይ የሚያርፍ የተፈጥሮ መዋቢያ፡፡ በተለይም ‹ባጠቋ›› ተብሎ የሚጠራውን ዛፍ ግንዱ ላይ በድንጋይ በመቀጥቀጥ የሚወጣውን ፈሳሽ ነው ጎፈሪያቸውን የሚቀቡት፡፡ ቅቤ ወይም ሌላ ሰው ሰራሽ መዋቢያ አጥተው አይደለም ይህን የሚመርጡት፤ የ‹‹ባጠቋው›› መዓዛ በአካባቢው ወንዶች አገላለጽ ‹‹ከፈረንሳይ ሽቶዎች ሁሉ ስለሚልቅ›› እንጅ፡፡ ጥሩው መዓዛ ደግሞ ከውቡ አለባበስና የበዓል ድባብ ጋር ተዳምሮ ጨዋታው ለሚከወንበት አካባቢ ልዩ ድባብ ይፈጥርለታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ተፈጥሯዊው ውብ መዓዛ ባልተበረዘው ባህል ላይ አርፎ ልዩ ገጽታ ስለሚሰጠው ነው፡፡

ነሀሴ 16 ወደ ዋግኽምራ ጎራ ያለ ሰው ታዲያ በሻደይ ጨዋታ ውበት ብቻ ሳይሆን ዘመን ባልከለሰው አክብሮታቸው እና ፍቅራቸው ተደንቆ፣ በደግነታቸውም አክብሮቱን ገልጾ ይመለሳል፡፡ ወንዶች ነሀሴ 15 ላይ አንድ ቀዳሚ ሥራ አላቸው፤ ለልጃገረዶቹ የሻደይ ቅጠሉን መቁረጥ፡፡ ቅጠሉን ማምጣቱ የወንዶች ሥራ ነው፤ የሚቆርጡትም በባዶ ሆዳቸው ነው፤ ቁርስ ሳይበሉ፡፡ ሻደዩን በሴቶቹ ወገብ ልክ በሚሆን ግምት በዛፎች ልጥ ያዘጋጁላቸዋል፡፡ የተዘጋጀውን ሻደይም ለልጃገረዶቹ በደስታ ይሰጧቸዋል፡፡ ‹‹ከዓመት ዓመት ያድርስህ!›› መባሉ የሚጀምረውም ያኔ ነው፡፡ ሴቶችም የተቀበሉትን ሻደይ በቀጥታ ወደቤታቸው ይዘውት አይገቡም፤ ይልቁንም ከቤታቸው ጓሮ ባለው ሳር የለበሰ ቦታ ላይ ያስቀምጡታል፡፡

ነሀሴ 16 ላይ ወንዶቹ በጠዋቱ ተጠራርተው ወደ ቆላማው አካባቢ በመሄድ በኽምጣጘ ቋንቋ ‹‹ጊጤ›› የሚባለውን ወፍራም፣ ደንዳና እና በውስጡ ከፍተኛ ውኃ የሚይዝ ግንድ ይቆርጣሉ፡፡ ከጊጤው ላይ የሚሰካ መፎካከሪያ ጦር ደግሞ ከዕጽዋት ሹል እያደረጉ ያዘጋጃሉ፡፡ ጊጤው ከእንጨት የተሰራው ጦር ሲያርፍበት በቀላሉ የሚበሳ ነው፡፡ ወንዶች እነዚህን ያዘጋጁና ሴቶቹ ለመንደርተኞቹ አማካኝ በሆነ ቦታ ‹‹ሻደይ!›› እያሉ ከሚጫወቱበት ቦታ ጦር እየመከቱ ጥንካሬያቸውን ይፈትናሉ፡፡ በትግል እና በንጥቂያ ውድድርም በልጃገረዶቹ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ይጥራሉ፡፡
ሴቶቹ ሲጫወቱ ውለው ሲመሽ ወደየቤታቸው ይሄዳሉ፤ ሌላ አካል እንዳይተናኮላቸው ደግሞ ወንዶቹ መከታ ሁነው ይጠብቃሉ፤ ወደ ቤታቸውም ያደርሳሉ፡፡


የሻደይ ጨዋታ ከነሀሴ 16 እስከ ነሀሴ 21 በዚህ መልኩ ሲከበር ሁሉም ውበቱን ተጠንቅቆ ይጠብቃል፤ ሳይደበዝዝም ሳምንቱን በሙሉ ይቆያል፡፡ በጊዜው የወንዶች ጀግንነት እና ኃላፊነትን የመወጣት አቅምም ይፈተሻል፡፡ በሴቶቹ ያልተመረጡ ወንዶች ያለፈቃዳቸው ሴቶችን እንዳይተናኮሉ በማድረግ በኩል የጠባቂ ወንዶቹ ሚና ከፍተኛ ነው፤ ጠባቂዎቹ የሻደይ ሴቶች ሰላም አስከባሪ ናቸውና፡፡

በሻደይ ጨዋታ ሌላም ትዕይንት አለ፡፡ ወንዶች ‹‹ከዓመት ዓመት ያድርሰን!›› በማለት የሻደይ ቅጠልን ከልጃገረዶች ወገብ ላይ ይቆርጣሉ፡፡ ወግ ደርሶት፣ እንዲያው ተሳክቶለት፣ የፍቅር ነገር ነካክቶት ከሆነ ወንዱ ከሚፈልጋት ሴት ወገብ ላይ የሻደይ ቅጠሉን ለመበጠስ ቀኑን ሙሉ ባይኑ እያማተረ፣ የከጀላትን ልጅ እየተከተለ ቀንቶት ሻደዩን ሲቆርጥ ፈገግ ብላ ካየችው ድል ማድረጉን ያረጋግጣል፡፡ ምንም ምላሽ ካላገኘ ደግሞ ከንቱ ድካም ስለሚሆንበት እጣ ፈንታውን በሌሎች ላይ መሞከር አለበትና ሳይረፍድበት ወዲያውኑ ምልስ ይላል፡፡

ሴቶቹ እና ወንዶቹ በሻደይ ሲደምቁ፣ ሲጨዋወቱ ይሰነብቱና በቆይታቸው ካገኙዋቸው በረከቶች ቀንሰው ነሀሴ 21 ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ፡፡ ቀሪውን ደግሞ ለምግብነት የሚውለውን አዘጋጅተው በጋራ ይመገባሉ፡፡ ከምግቡ በፊት ግን አንድ መከወን ያለበት ባህላዊ ጨዋታ አለ፡፡ በቂጣ፣ በቅቤ፣ በአይብ፣ በጨው… የሚሠራ ‹‹አስኩር›› የሚባል ምግብ ሴቶች ከቤት ውስጥ ሰርተው ወንዶች እንዳያገኙት ይደብቁታል፡፡ ወንዶች ወደ ቤት እንዳይገቡም ከበር ላይ ሆነው ይከላከላሉ፡፡
ወንዶችም አስኩሩን ለማግኘት ብርቱ ትግል ያደርጋሉ፤ ካገኙት በኋላም በደስታ ተሻምተው ይበሉታል፤ ሌላው ምግብም በስርዓት መሠጠት ይጀምራል፡፡
ዝግጅቱ ሲጠናቀቅም ልጃገረዶቹ እና ወንዶች በሻደይ ጨዋታው ጊዜ ያጠፉት ጥፋት ካለ ይቅርታ በመጠያየቅ ‹‹ከዓመት ዓመት ያድርሰን›› በማለት ለቀጣይ ዓመት ጨዋታ ቃል ገብተው ይለያያሉ፡፡

በእነዚህ የሻደይ ወቅቶች የተጠነሰሰ ፍቅር ካለ ደግሞ የሽምግልና ስርዓቱ እንዲቀጥል ሆኖ ወደ ትዳር ይሻገራል እላችኋለሁ! እመወዳችሁዋ!

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.