<> Skip to main content
በጎ ፈቃደኞች ከ1ሺህ 200 በላይ ሰዎችን ህይወት ሊታደግ የሚችል ደም ለገሱ፡፡

 

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 02/2011 ዓ.ም (አብመድ)በጎ ፈቃደኞች እየለገሱት ያለው ደም በክረምት ወቅት የሚከሰተውን የደም እጥረት ለመቅረፍ እያገዘው መሆኑን የደብረ ማርቆስ ደም ባንክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ደም ባንክ አገልግሎት ባሳለፍነው ሐምሌ ብቻ ከ405 በላይ ዩኒት ደም ከበጎ ፍቃደኞች እንደተሰበሰበ የደም ባንክ አገልግሎቱ ኃላፊ አቶ ከፋለ ገበየሁ ገልጸዋል፡፡ አንድ ዩኒት ደም እስከ ሦስት ሰዎችን ሕይወት እንደሚታደግ ይታመናል፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት 405 ዩኒት ደም የ1ሺህ 245 ሰዎችን ህይወት ያተርፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በጎ ፈቃደኛች ደም የለገሱትም ከምስራቅ ጎጃም ዞንና ከምዕራብ ጎጃም ደግሞ ከፍኖተ ተሰላም፣ ከፈረስ ቤት እና ከቡሬ መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ከፋለ መረጃ የደም አቅርቦቱ በአብዛኛው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በክረምት ወራት ከፍተኛ የደም አቅርቦት ችግር ይከሰት ነበር፡፡
በዚህ ክረምት ግን ሌሎች በጎ ፈቃደኞችም ደም የመለገስ ልምድ እያዳበሩ እንደሆነ ነው ኃላፊው የነገሩን፡፡ ይህም በክረምት ወራት የሚፈጠረውን የደም እጥረት ለመቅረፍ እያገዘ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻክል ወረዳ በአማኑኤል ከተማ በጎ ፈቃደኞች ካለፈው ሰኞ እስከ አርብ ድረስ ደም ለግሰዋል፡፡ የወረዳው የሥራ ኃላፊዎችም በደም ልገሳ ተግባሩ ተሳትፈዋል፡፡ የማቻክል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ሙሉሀብት የሥራ ኃላፊዎች ደም መለገሳቸው የዜጎችን ህይወት በመታደግ በጎነትን በተግባር ለማሳየት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ በደም እጦት ሊጠፋ የነበረ ህይወትን ማዳን የሚያስገኝላቸው የህሊና እርካታ ከፍተኛ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡

ሌላዉ በጎ ፈቃደኛ ወጣት አብርሃም ቢተው ለሦስተኛ ጊዜ ደም መለገሱን ነግሮናል፡፡ ከዚህ በፊት በለገሰው ደም ያለምንም ወጪ የሰዎችን ሕይወት መታደጉ በበጎ ተግባሩ እንዲቀጥልበት እንዳነሳሳውም ነው የተናገረው፡፡ በድንገተኛ አደጋዎች እና በህመም፣ እናቶች ደግሞ በወሊድ ወቅት በሚፈስሳቸው ደም ምክንያት ህይወታቸውን እንዳያጡ እያደረጉ መሆኑ ደግሞ እርካታውን ከፍተኛ እንደሚያደርግላቸው በጎ ፈቃደኞቹ ተናግረዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ደም ባንክ አገልግሎት በ2011 በጀት ዓመት ከ6 ሺህ በላይ ዩኒት ደም ሰብስቦ ለ12 ሆስፒታሎች በማቅረብ የዜጎችን ህይወት እየታደገ ነው። ደም ባንኩ በምስራቅ ጎጃም ዞን ለሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎች፣ በምዕራብ ጎጃም ደግሞ ለፈረስ ቤት፣ ለፍኖተ ሰላም እና ለቡሬ ሆስፒታሎች ያቀርባል፡፡

መረጀውን ያደረሰን ጋሻዬ ጌታሁን ነው፡፡

Image