<> Skip to main content
ከ4 መቶ ዓይነት በላይ ጸረ ተባይ ኬሚካሎች አልተወገዱም፡፡

 

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 03/2011 ዓ.ም (አብመድ) የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ጸረ ተባይ ኬሚካች በክልሉ እንደሚገኙ የአማራ ክልል የእጽዋት ዘር እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ኳራንታይን ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ኬሚካሎችን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ደንብ ወጥቷል፤ በተያዘው ዓመት ጸድቆ ተግባራዊ ይሆናል፤ መመሪያም እየተዘጋጀ ነው ብሏል፡፡
በጸረ ተባይ ኬሚካሎች ላይ በተገቢው መንገድ ክትትል እየተደረገ እንዳልሆነ የአማራ ክልል የእጽዋት ዘር እና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ኳራንታይን ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የባለስልጣኑ የዕጽዋት ጤናና ምርት ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አበባው አዳነ እንደተናገሩት ለሰው እና ለእንስሳት አደገኛ የሆኑ ወደ መርዛማነት የተቀየሩ፣ ከ30 አመት በላይ የተቀመጡ ኬሚካሎች አልተወገዱም፡፡ ኬሚካሎቹ በአብዛኛው በግብርና መጋዝኖች፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ተቀምጠው እንደሚገኙ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የዕጽዋት ጤና ጥራት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ወልደ ሀዋሪያት አሰፋ የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጀ 674/2002 ቢወጣም የአፈፃጸም ደንብ እና መመሪያ ባለመኖሩ ኬሚካሎችን መቆጣጠር አልተቻለም ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ጸረ ተባይ ኬሚካሎችን ለመቆጣጠር እና ለመከታተል በተያዘው ዓመት ጸድቆ ተግባራዊ የሚሆን ደንብ ወጥቷል፤ መመሪያም በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ኬሚካሎችን እንዲከታተሉ እና እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የክልል ቢሮዎች ጋርም በየጊዜው ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ጸረ- ተባይ ኬሚካሉን ለመቆጣጠር እና ለመከታተል ደንብ እና መመሪያ አለመውጣቱ በውይይቶች እንደችግር ተነስቷል፡፡ ከክልሎች ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሠራር ችግር እንደነበረበትም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

ክልሎች የጸረ ተባይ ኬሚካሎች በተገቢው መንገድ አገልግሎት ላይ መዋላቸውን እና በተገቢው መንገድ መቀመጣቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለባቸው በአዋጁ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጅ በተገቢው መንገድ ክትትል እና ቁጥጥር እየተደረገ እንዳልሆነ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡ የኬሚካሎች ክምችት የሚፈጠረው ከአቅም በላይ ግዥ በመፈጸሙ ሳይሆን የሚቀርበው ባለፈው ዓመት ጥቅም ላይ የዋለውን የኬሚካል መጠን እና የሚትዮሮሎጅ ትንበያን መሠረት ተደርጎ በመሆኑ የተባይ ክስተቱ ሊቀያየር ስለሚችል የተገዛው ኬሚካል ጥቅም ሳይሰጥ የአገልግሎት ጊዜው ስለሚልፍ እንደሆነም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

የአገልግሎት ጊዜያቸው የተቃረቡ ጸረ ተባይ ኬሚካሎች እንዳይገዙ ለለመቆጣጠርም ተመርተው 6 ወር ያለፋቸው ኬሚካሎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ አዋጁ ከልክሏል፡፡ ጸረ ተባይ ኬሚካሎች ከአውሮፓ ሀገራት፣ ከቻይና እና ከህንድ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ማሟላታቸው ተረጋግጦ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ የአንበጣ፣ የተምች እና የግሪሳ ወፍ መከላከያ ኬሚካሉ በግብርና ሚኒስቴር በኩል እንደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡ ከዚህ ወጭ ያሉት ጸረ ተባይ ኬሚካሎች ፈቃድ ባላቸው ከፍተኛ ባለሀብቶች፣ የግል ድርጅቶች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት እንዲገቡ እየተደረገ እንደሆነ ነው አቶ ወልደ ሀዋሪያት የተናገሩት፡፡

ጸረ ተባይ ኬሚካሎች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማስተዳደር እና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ኬሚካሎችን ያስገባው አካል ነው፡፡ ክልሎችም የክትትል እና የቁጥጥር የአቅም ግንባታ ሥራ እንዲሰሩ በአዋጁ እንደተቀመጠ አቶ ወልደ ሃዋሪያት ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ፡-ዳግማዊ ተሰራ

 
Image