<> Skip to main content
‹‹ዋካንዳ››ን በባሕር ዳር የመገንባት ህልም

‹‹ዋካንዳ››ን በባሕር ዳር የመገንባት ህልም በሀሳብ የቀረበ እንጅ ሙሉ ጥናቱ የተጠናቀቀ እንዳልነበር ተገለፀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2011 ዓ.ም (አብመድ) ምናባዊውን ዋካንዳ በአማራ ክልል ጭስ አባይ አካባቢ ዕውን ያደርጋል የተባለው ፕሮጀክት የት ደረሰ?

Image may contain: outdoor

‘ምንጩ’ በሚል ስያሜ በጭስ አባይ ፏፏቴ አቅራቢያ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መንደር ሊገነባ እንደነበር በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡ ይታወቃል፡፡ ይገነባል ተብሎ የታሰበው የቴክኖሎጂ መንደር ባለቤት ሀብ ሲቲ ላይቭ የተባለ የአሜሪካ ድርጅት ነው፤ እ.አ.አ በ2018 በሆሊውድ ፊልም መንደር ተሠርቶ ለዕይታ የበቃው የ‹‹ብላክ ፓንተር›› ፊልም ምናባዊ ከተማ ዋካንዳን መሠረት አድርጎ እንደሚገነባ ነበር በወቅቱ የተገለጸው፡፡

ሀብ ሲቲ ላይቭ የተባለው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሚካል ካሚል ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ የፕሮጀክቱ ስያሜ ‘ምንጩ’ እንደሚባልና ለ20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ኢትዮጵያንም በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ደረጃ እንደሚያሰጣት ነበር የተናገሩት፡፡ ፕሮጀክቱ እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅና ሦስት ቢሊዮን ዶላር በወቅቱ ተመድቦ እንደነበርም መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ቀሪው በጀት በዋናነት ከአሜሪካ ባንኮች እንደሚገኝም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመው ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ፕሮጀክቱን እና ተያያዥ ሥራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውንም በቃለ መጠይቁ አስረድተው ነበር፡፡ ባሕር ዳር የጣና ሐይቅ እና የጭስ የአባይ መገኛ ውብ ከተማ በመሆኗ ተመራጭ አድርጓታል፤ ከታሪክ አንፃርም የዓለም ትልቁ ስልጣኔ መነሻ ከዚህ አካባቢ ነው ተብሎ ስለሚታመን ምናባዊ ዋካንዳ የቴክኖሎጂ ከተማን ለመገንባት አካባቢውን እንደመረጡት ሥራ አስኪያጁ እንደመረጡት መናገራቸውም ይታወሳል፡፡

ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ አድርጎት የነበረው ደግሞ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ከተማን የመስራት እቅዱን አስመልክቶ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከባለድርሻዎች ጋር ውይይት ማድረጉን ተከትሎ አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ሽፋን መስጠታቸው ነው፡፡ ሀብ ሲቲ ላይቭ የተባለው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሚካል ካሚል እውነተኛውን የዋካንዳ ፕሮጀክት በጭስ ዓባይ ፏፏቴ አቅራቢያ ገንብቶ ለመጨረስ ከስምንት እስከ አስር ዓመታት እንደሚወስድ፣ ፕሮጀክቱንም አጠናቅቀው ዕውን እንደሚደርጉት ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ሀሳባችን በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ለምንጠይቀው ሁሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገልን ነው›› ብለውም ነበር፡፡
አብመድ ‹ዕውን ይሆናል የተባለው ምናባዊው ዋካንዳ› የት ደረሰ? በማለት ስለ ፕሮጀክቱ እውነተኛነት ጠይቋል፡፡

የቀድሞው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የአሁኑ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ “የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የፕሮጀክቱ እውን መሆን ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወሳኝ በመሆኑ ተገቢውን ድጋፍ እንድናደርግ ደብዳቤ ፅፎልን እንጅ በኛ በኩል ስለ ፕሮጀክቱ የምናውቀው ነገር አልነበረም” ብለውናል፡፡ በተፃፈለት የድጋፍ ደብዳቤ መሠረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በንድፈ ሀሳቡ ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ማድረጉንም አስታውሰው ውይይቱም ፕሮጀክቱ ለሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር በሚኖረው ፋይዳ ዙሪያ እንደነበር እና አሁን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እውቅና እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶክተር ሂሩት ካሳሁን በበኩላቸው ስለ ደብዳቤው ምንም አይነት እውቅና እንደሌላቸው እና እርሳቸውም እንዳልፃፉ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጌታሁን መኮንን በበኩላቸው በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዳራሽ የፕሮጀክቱ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት እንጅ ጥናቱ ተጠናቅቆ የቀረበ እንዳልነበር ነው ያስረዱት፡፡ የቀረበውን ሀሳብ መሠረት በማድረግም ቢሮው ሙሉ ጥናቱ መቅረብ እንዳለበት ‹‹ሀብ ሲቲ ላይቭ›› ለተባለው ድርጅት ሀሳብ አቅርቦ ነበር፤ ነገር ግን ድርጅቱ እስካሁን ጥናቱን አጠናቅቆ አለማቅረቡን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ሊተገበር የሚችል ማንኛውም የኢንቨስትመንት ጥያቄ በሀሳብ ደረጃ ከቀረበ በኋላ አዋጭነቱ ሳይገመገም ወደ ስራ እንደማይገባ ዶክተር ጌታሁን አስገንዝበዋል፡፡ አብመድ የፕሮጀክቱን ባለቤት ‹‹ሀብ ሲቲ ላይቭ›› ሥራ አስኪያጅን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

ፎቶ፡- ከድረ ገጽ

Image