<> Skip to main content
ሳዑዲ አረቢያ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ የሃጅ ተጓዦችን ተቀብላለች፡፡

 

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2011 ዓ.ም (አብመድ) ሳዑዲ አረቢያ ከዕቅዷ በላይ የሀጅ ተጓዦችን እያስተናገደች መሆኗ ተዘገበ፡፡

Image may contain: sky and outdoor

ሀገሪቱ ኢቦላን በመስጋት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጓዦችን እንደማትቀበል አስታውቃለች፡፡ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞች በሃጅ ሀይማኖታዊ ስነ-ስርዓት ለመሳተፍ ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል፡፡ የሳዑዲ ሃጂ ሚኒስቴር እንደጠቆመው 1 ሚሊዮን 843 ሽህ 961 የኃይማኖቱ ተከታዮች በሀይማታዊ ክዋኔው ለመታደም ወደ ሀገሪቱ ደርሰዋል፡፡ እንደ ሀገሪቱ ብዙኃን መገናኛ ከሆነ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን አማኞች በሀይማኖታዊ ስነ-ስርዓቱ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ነው የታቀደው፡፡

በምዕራብ ሳዑዲ አረቢያና በሀገሪቱ ቅዱስ ከተማ ከአምስት ቀናት በላይ ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ስርዓቶች ይከወናሉ፡፡ በየዓመቱ ከአፍሪካ ሀገራትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ይጎርፋሉ፡፡ ከሰሜን አፍሪካ ሀገራት ግብፅ፣ አልጄሪያና ሞሮኮ ከፍተኛ ተጓዦች አሏቸው፡፡

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ናይጄሪያ ከፍተኛውን የተጓዦች ቁጥር ትይዛለች፡፡ እ.አ.አ በ2017 ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር 79 ሺህ ተጓዦች ወደ ሳዑዲ አቅንተዋል፡፡ በተጠቀሰው ዓመት የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ተጓዦችን በመላክ ከ1 እስከ10 ያለውን ደረጃ ይዘው እንደነበርም ይታወሳል፡፡

በዚህ ዓመት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጓዦች ወደ ሳዑዲ እንዳይገቡ እገዳ ተጥሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኢቦላ በሽታ ስለተከሰተባት ነው፡፡ በጣም በፍጥነት ተላላፊው ኢቦላ ለነዋሪዎቿ እና ለምዕመናኑ ሥጋት እንዳይሆን፣ ጤናቸውንም ለመጠበቅ በማሰብ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በኪሩቤል ተሾመ

ምንጭ፡- አፍሪካ ኒውስ

Image