<> Skip to main content
ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በማሰብ መከበር አለበት::

በወልድያ ከተማ የኢድ አል አድሐ በዓል አከባበር ላይ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ስጦታ አበረከቱ፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2011 ዓ.ም (አብመድ) 1440ኛው የኢድ-አል-አድሐ (አረፋ) በዓል በወልድያ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡

በበዓሉ ሶላት ተሳታፊ የነበሩት የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሐመድ ያሲን ‹‹አረፋ የመሰዋዕትነትና የመዳን በዓል በመሆኑ የተፈናቀሉ እና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በማሰብ መከበር አለበት›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ በዘመናት አብሮነት ታሪኩ ውስጥ ያሉትን መቻቻል፣ መተዛዘን፣ መረዳዳት ያላቸውን ፋይዳ በመረዳት በዓሉን እንዲያከብርም ከንቲባው አሳስበዋል፡፡

በሰው ልጅ የዘመናት ጥረት እና ድካም የተዘረጉትን መልካም እሴቶች ኃላፊነት የማይሰማቸው አካላት በአንድ ጀንበር እንዲንዷቸውና ወደ ሥስዓት አልበኝነት እንዲቀይሯቸው መፍቀድ እንደማይገባም ከንቲባው በመልዕክት አሳስበዋል፡፡

የሃይማኖቱ ተከታዮች እንደ አንድ ሕግ አክባሪ ዜጋ መልካም ተግባርን የመውደድ፣ ክፋት፣ ንትርክ እና መጠላለፍን የማውገዝ ኃላፊነት እንዳለባቸውም በመልእክታቸው አስገንዝበዋል፡፡

“እስልምና ተንኮል፣ በቀል፣ ጥላቻ፣ መገዳደልን ያወግዛል” ያሉት ከንቲባው እስልምና ሠላም፣ አንድነት፣ መረዳዳት፣ መከባበር እና መተዛዘን ማለት በመሆኑ ይህንን መልካም እሴት በማጎልበት ለከተማዋ ልማት በጋራ መረባረብ እንደሚገባም መልዕክት ተላልፏል፡፡

 

በበዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓቱ የወልድያ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ክርስቲያኖችን በመወከል አቶ ታከለ ንጉሤ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያለው የአበባ ስጦታ አበርክተዋል፡፡ በሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከዚህ ቀደምም ስጦታ የመለዋወጥ ሥርዓት ለዘመናት ሲከናወን ነበር፤ ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በፊት ተቋርጦ እንደነበርና እንደገና እንደተጀመረ ተገልጿል፡፡

የወልድያ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ደግሞ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮቹ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ላበረከቱት አስተዋጽኦ የዕውቅናና የምሥጋና የምሥክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ባለ ዓለምዬ -ከወልድያ

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.