<> Skip to main content
የመሰዋዕትነት በዓል::

‹‹ኢብራሂም… ኢብራሂም… ታላቅነትህን አስመስክረሀልና እርዱን አቆየው!›› ይህ በአረፋ ተራራ የተሰማው የመልክተኛው ጅብሪል ድምፅ ነበር፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2011 ዓ.ም (አብመድ) የኢድ አልአድሐ በዓል ‹‹የመሰዋዕትነት በዓል›› በመባልም ይታወቃል፡፡ የኢድ አል አድሐ በዓል የሚከበረው በሒጅራ ዘመን አቆጣጠር ዓረፋ የሚውልበት ወር በገባ በአሥረኛው ቀን ነው፡፡ በአሥራ ሁለት ወራት የሚከፋፈለው የሒጅራ አቆጣጠር 354 ወይም 355 ቀናት አሉት፡፡ በየዓመቱ የአሥር ቀናት ለውጥም አለው፡፡ ከጨረቃ መውጣት ጋር ተያያዥነት ስላለውም እንደ ኢድ አል አድሐ ያሉትን የሙስሊም በዓላት ለማክበር ትክክለኛውን ቀን አስቀድሞ ማወቅ ቀላል አይደለም፤ ምክንያቱም ቀናቱ የሚወሰኑት ከጨረቃ መውጣት ጋር ተያይዞ ነውና፡፡ የዘንድሮው 1440ኛው የኢድ አልአድሐ በዓል በፀሐይ አቆጣጠር ነሐሴ 5 ቀን 2011 ዓ.ም በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው፡፡ በዓሉ በቅድስቲቱ ከተማ መካም ከመላው ዓለም በተሰባሰቡ ከ2 ሚሊዮን በላይ አማኞች በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

Image may contain: one or more people and outdoor

ለመሆኑ የኢድ አልአድሐ በዓል በእስልምና ሃይማኖታዊ አስተምህሮ እንዴት ይታይ ይሆን? ስንል ከ20 ዓመታት በላይ በሃይማኖታዊ አስተምህሮው የዘለቁትን ዑስታዝ ባሕሩ ዑመርን አነጋግረናቸዋል፡፡

የኢድ አልአድሐ በዓል በስተርጅና በመጣ የልጅ ፍቅር ከፈጣሪያቸው ፍቅር በትንሹም ቢሆን የራቁት ነብዩ ኢብራሂም ወደ ነበሩበት የአሏህ ፍቅር ከፍታ የተመለሱበት፤ ይህንንም በሚወዱት የልጃቸው ሕይወት ላይ ተፈትነው ማለፋቸውን ያረጋገጡበት ‹‹የመሰዋዕትነት በዓል›› ነው ያሉት ዑስታዝ ባሕሩ በተለምዶ የአረፋ በዓል ይባላል እንጂ አረፋ የፈተናው ተራራ ሲሆን በዓሉ ‹‹ኢድ አልአድሐ›› ነው የሚባለው ብለውናል፡፡

በኢድ አልአድሐ በዓል ወቅት ከሚጎበኙ ቦታዎች መካከል አንዱ የዓረፋ ተራራ ነው፡፡ ቦታው ለኢድ አልአድሐ በዓል መሠረት የሆነ እና በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ ገድል የተሠራበት ተራራ ነው፡፡ ነብዩ መሐመድ (ሱ.ወ) ከተወለዱባት ቅድስቲቱ የመካ ከተማ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከነቢዩ መሐመድ ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ነቢዩ ኢብራሂም ከፈጣሪ የቀረበላቸውን ትልቅ ፈተና በድል የተወጡበት ተራራ ነው፡፡ ነብዩ ኢብራሂም ለልጅ ከፍተኛ ጉጉት ቢኖራቸውም ልጅ ሳያገኙ ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል፡፡ ከጾም ጸሎት በኋላ ግን በዕድሜያቸው ማምሻ ላይ አንድ ልጅ አገኙ፤ ስሙንም ኢስማኤል አሉት፡፡ በዕድሜያቸው ማምሻ ላይ ስለመጣም አብዝተው ይወዱት ነበር ብለዋል ዑስታዝ ባሕሩ፡፡

ነብዩ ኢብራሂም በስተርጅና ባገኙት ልጅ በጣም ደስተኛ የነበሩ ቢሆንም ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው፡፡ አንድ ቀን ፈጣሪ ልጃቸውን ኢስማኤልን እንዲሰውለት ሲጠይቃቸው በሕልም ታያቸው፡፡ ፈጣሪያቸውን አብዝተው ለሚወዱት ነቢዩ ኢብራሂም ጉዳዩ ከሕልም በዘለለ ትርጉም ነበረው፡፡ ልባቸው ክፉኛ ቢያዝንም ኢስማኤልን ለመሰዋት ወሰኑ፡፡ ውሳኔያቸውንም ለልጃቸው ነገሩት፡፡ የፈጣሪ ፍላጎት ከሆነ ራሱን መሰዋዕት አድርጎ ለማቅረብ በሐሳባቸው ተስማማ፡፡

Image may contain: one or more people, crowd and outdoor

አባትና ልጅ የፈጣሪን ትዕዛዝ ለመፈፀም ከቅድስቲቱ የመካ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው የዓረፋ ተራራ አቀኑ፡፡ በየመንገዳቸው ለሦስት ጊዜያት ያክል የገጠማቸውን የሰይጣን ፈተና ተቋቁመው እና በመጨረሻው ፈተና ሰይጣንን ከእነሱ እንዲርቅ በጠጠር አባረው ከተራራው አናት ላይ ደረሱ፡፡ ዛሬም ድረስ በኢድ አልአድሐ በዓል ዋዜማ ወደ አረፋ ተራራ የሚወጡ ሐጃጆች አባት እና ልጅ ሰይጣንን ድል ያደረጉበትን መንገድ ለማስታወስ ጠጠር የመወርወር ሥርዓት ያካሂዳሉ፡፡

‹‹ነብዩ ኢብራሂም ከተራራው አናት ከደረሱ በኋላ ኢስማኤልን ለማረድ ተዘጋጁ›› ያሉት ዑስታዝ ባሕሩ ነገር ግን ድርጊቱ ለነብዩ ኢብራሂም ቀላል እንዳልነበረም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሐሳባቸውን ቀይረው ሁለት ሦስት ጊዜያት ያህል ከተራራው ወርደው ነበር፤ ይሁንና የፈጣሪ ትዕዛዝ ከልጃቸው እንደማይበልጥ በማሰብ ቢላውን ከልጃቸው አንገት ላይ አሳረፉት፡፡ በቀላሉ ሊታረድላቸው ግን አልቻለም፡፡ በዚህም ጊዜ አንድ ተአምር ተፈጠረ›› ብለዋል፡፡

ከወደ ሰማይ ያልተጠበቀ ጥሪ ተሰማ፡፡ ‹‹ኢብራሂም…ኢብራሂም… ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው›› ተባሉ፡፡ ድምፁ የመላእክተኛው ጅብሪል ነበር፡፡ በኢስማኤል ምትክም መልአኩ ከገነት ያመጣውን በግ እንዲያርዱና ልጁን ወደቤቱ እንዲመልሱ ነገራቸው፡፡ በኢስማኤል ትክ ከሰማይ የወረደው በግ ታረደ፡፡ የነብዩ ኢብራሂም የፈጣሪ ፍቅር፤ የኢስማኤል ታዛዥነት በአረፋ ተራራ ተፈትኖ አለፈ፡፡ ኢብራሂም ለፈጣሪያቸው ኢስማኤል ለአባቱ ተገዥነታቸውን አስመስክረው በአሏህ ዘንድ ሞገስን አገኙ፡፡ አባት እና ልጅ ለፈጣሪ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል አድሐ በዓል ሆና እንድትከበርም ተወሰነ፡፡

ኢስማኤል ለመሰዋዕትነት መቅረቡ ለ‹‹ኡድሒያ›› መነሻ በመሆኑ በዓሉን የእርድ በዓል አድርጎታል፡፡ ኢድ አልአድሐ የመሰዋዕትነትና የመዳን በዓል ነው፡፡ የሐጅ ጸሎት የሚፈፅሙ በዚህ ዕለት ‹‹ኡድሒያ›› የማረድ ግዴታ አለባቸው፡፡ ወደ ሐጅ ያልሄዱ ደግሞ ከተቻለ በዚሁ ዕለት በየቤታቸው እንስሳ በማረድ ‹‹ኡድሒያ›› ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ታዲያ ‹‹ኡድሒያ›› ተብሎ የሚመዘገበው ለ‹‹ኡድሒያ›› ከታረደው ሥጋ አንድ ሦስተኛው በቀጥታ ለድሆች ሲከፋፈል፣ አንድ ሦስተኛው ለዘመድና ለወዳጅ ሲሰጥ፣ የቀረው አንድ ሦስተኛው ደግሞ ለቤተሰቡ አገልግሎት ሲውል ብቻ መሆኑን ዑስታዝ ባሕሩ ነግረውናል፡፡
ኢድ ሙባረክ!

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው 
ፎቶ፡- በአሊ ይመር -ከደሴ

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.