<> Skip to main content
አትክልት በል መሆን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አስተዋጽኦ እንዳለው ተገ

አትክልት በል መሆን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2011 ዓ.ም (አብመድ) ከዚህ ቀደም የምንሰማው የዕፅዋት ተዋፅዖዎችን መመገብ ለጤና ጠቃሚ መሆኑን ነበር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እንስሳትንና የእንስሳት ተዋፅዖን መመገብ የጭካኔ ምልክት አድርገው በመቁጠር ወይም ሃይማኖታዊ ምክንያት በማቅረብ የዕፅዋት ውጤቶችን ብቻ መመገብን ይመርጣሉ፡፡ እነዚህ የዕፅዋት ውጤቶችን ብቻ የሚመገቡ ሰዎችም አትክልት በል (ቪጂቴሪያን) የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከሰሞኑ ቢቢሲ በሳይንስና አካባቢ ዓምዱ ባወጣው መረጃ መሠረት ደግሞ አትክልት በል መሆን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አስተዋጽኦ አለው፡፡ ቢቢሲ ዋቢ ያደረገው ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎችን ሪፖርት ነው፡፡

ባለሙያዎቹ እንዳሉት ምዕራባውያን በብዛት የእንስሳት ተዋፅዖዎችን ስለሚመገቡ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ባለሙያዎቹ ‹‹ሰው ሁሉ አትክልት በል ይሁን›› የሚል ምክረ ሐሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹ሰዎች የእንስሳት ተዋፅዖዎችን መብላት ቢያቆሙ በአነስተኛ መሬት ብዙ ምግብ ማምረት ይችላሉ›› የሚል ገራገር ምክረ ሐሳብ ብቻ ነው ያስቀመጡት፡፡ በእርግጥ የእንስሳት ፅዳጅ ለከባቢ አየር መበከል ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም በርካታ ጥናቶች ከዚህ ቀደም አሳይተዋል፡፡

የመንግሥታት የጋራ የአየር ንብረት ለውጥ ጥምረት አባላት የሆኑ 107 ተመራማሪዎች ያሰናዱት ሰነድ እንደሚያመለክተውም መሬትን በአግባቡ ምርታማ አድርጎ መጠቀም ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ መቀነስ ያስችላል፡፡ ሰነዱ በስዌዘርላንድ ጀኔቫ ውይይት እንደተደረገበትም ታውቋል፡፡

ፕሮፌሰር ፔት ስሚዝ የተባሉ የአካባቢ ሳይንስ ተመራማሪ ‹‹እኛ ሰዎችን ስጋ አትብሉ አንልም፤ ምክንያቱም ለአንዳንዶች ብቸኛ ምግባቸው ስጋ ሊሆን ስለሚችል፡፡ ነገር ግን ምዕራባውያኑ ከሚገባው በላይ ስጋ እየበላን ነው›› ብለዋል፡፡ የባለሙያዎቹ ቡድን ሰነድ እንደሚያሳየውም ምዕራባውያኑ ብዙ የእንስሳት ተዋፅዖ መመገባቸው ብቻ ሳይሆን ብዙ አትርፈው ስለሚተው ለአየር ንብረት ለውጥ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ በምዕራባውያኑ ከሚከሰተው የአየር ብክለት ከ8-10 በመቶ የሚሆነው በምግብ ተረፈ ምርት መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

a

ሪፖርቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል፤ በተለይ የአፈር መሸርሸር እና የደን መመናመን ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው ያስጠነቀቀው፡፡

በተለይ ደግሞ ‹ለኃይል ምንጭነት› (ለከሰልና ለነዳጅ ምርት) በሚል ዛፎችን የሚያለሙ መንግሥታት ለምግብ ሰብል ማምረቻ የሚሆነውን መሬት ጭምር እየተሻሙ ስለሆነ በገደብ እንዲጠቀሙ ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ልክ በኢትዮጵያ የጤፍ ማሳ ለከሰል የሚውል ባሕር ዛፍና ግራር (ዲከረንስ) እንደሚለማበት ያለውን ማለተት ነው፡፡

የመሬት አጠቃቀም ሁኔታው የዓለምን ሁለንተናዊ ሁኔታ የሚወስን መሆኑን ያመለከተው የባለሙዎቹ የጥናት ሪፖርት በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባ ነው ያሳሰበው፡፡ ‹‹ከባቢ አየር የምንሰጠውን እየመለሰልን ነው፤ በካይ ጋዝን ስንለቅ ብክለትን፣ ስንንከባከበው ፀጋን እየሰጠን ነው›› ብለዋል ባለሙያዎቹ፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.