<> Skip to main content
‹‹ለግል ትምህርት ቤቶች የወጣው መመሪያ አገልግሎቱንና ክፍያውን ተመጣጣኝ

‹‹ለግል ትምህርት ቤቶች የወጣው መመሪያ አገልግሎቱንና ክፍያውን ተመጣጣኝ ያደርገዋል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡›› የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2011 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አልማዝ በየነ ሁለት ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ያስተምራሉ፤ በየዓመቱ የሚደረገው የክፍያ ጭማሪ ግን አቅማቸውን ያገናዘበ እንዳልሆነ ነው የገለጹት፡፡ ወይዘሮ አልማዝ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት የግል ትምህርት ቤት በየዓመቱ ለአንድ ተማሪ በአማካይ ከ50 እስከ 100 ብር የክፍያ ጭማሪ ያደርጋል፤ ‹‹ይህ ትክክል አይደለም›› ብለዋል ወይዘሮ አልማዝ፡፡

የትምህርት ቤት ክፍያ ግን ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ ሕይወትን ከባድ አድርጎባቸዋል፤ ለምዝገባ ሲሄዱ መጨመሩ ይነገራቸዋል፤ በትምህርት መካከል ላይም የክፍያ ጭማሪ በወረቀት ብቻ ተጽፎ መልዕክት እንደሚደርሳቸው ያስታወቁት ወይዘሮ አልማዝ መንግሥት መፍትሔ እንዲያበጅለት አሳስበዋል፡፡

አቶ ማስተዋል እንዷለም ደግሞ የመንግሥት ሠራተኛ ናቸው፡፡ በሚያገኞት ደመወዝ አብቃቅተው ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ያስተምራሉ፡፡ አቶ ማስተዋል ‹‹ትምህርት ቤቶቹ የሚያደርጉት የክፍያ ጭማሪ ትክክል አይደለም፤ በሦስትና ስድስት ወር ሁሉ የሚጨምሩ ትምህርት ቤቶች አሉ፤ ክፍያ ቋሚ የሚሆንበት መንገድ መፈጠር አለበት›› ብለዋል፡፡

በአሰገደች ደገፉ መታሰቢያ የግል ትምህርት ቤት የዳይሬክተሮች ዳይሬክተር አቶ ጎሹ ከበደ ያለውን የገበያ ሁኔታ በማጥናት ትምህርት ቤቱ ኪሳራ ላይ እንዳይወድቅ የክፍያ ጭማሪ ይደረጋል፤ ሒሳቡ ሲሰላም የመምህራን ደመወዝ ግንዛቤ ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከክፍያ ጭማሪ ውሳኔ በፊት ወላጆች ይሁንታቸውን እንዲሰጡ የሚሞላ ቅጽ በልጆቻቸው አማካኝነት ይላካል፤ አብዛኞቹ ቅሬታ ካላቀረቡ ይተገበራል፤ ለቀጣዩ ዓመትም የ90 ብር ጭማሪ ተደርጓል፤ ነገር ግን ደብዳቤ በመላክ ብቻ ነው የተፈጸመው›› ብለውናል፡፡ ይህ አሠራር ተቃውሞ እንዳልገጠመው ያስታወቁት ዳይሬክተሩ ‹‹በጉዳዩ ዙሪያ ከዚህ በፊት ወላጆች ተጠርተው ለማወያዬት ተሞክሯል፤ ለውይይት የሚገኙት ግን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው›› ብለዋል፡፡

‹‹እንደ ወላጅ የክፍያ ጭማሪ በዚህ ዓይነት መልኩ መቀጠል አለበት ብዬ አላስብም›› ያሉት ዳይሬክተሩ ኅብረተሰቡ የግል ትምህርት ቤት ከፍሎ ልጆቹን የሚያስተምርበት ደረጃ ላይ እንደማይኝና በሌላ በኩል አንደ የንግድ ሥራ በመሆኑ ትርፍ ማግኘት የግድ ስለሚል ፈሩን ሳይለቅቅ በውድድርና በነፃ ገበያ መመራት እንዳለበት፤ መንግሥትም ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚኖርበት አስንዝበዋል፡፡ 
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የቁጥጥርና ክትትል ኃላፊ (ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር) አንማው ቢዘንጋው የግል ትምህርት ቤቶች በምን መነሻ ሒሳብ እንደሚጨምሩ ግልፅ አለመሆኑን ተናረዋል፡፡ ‹‹ከቢሮ ጀምሮ ዞንና ወረዳ ድረስ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት አልነበረውም፤ ልቅ ሁኔታ ነበር፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን የማኅበረሰቡም ቅሬታ እየጠነከረ ሲመጣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከሌሎች ክልሎች ልምድ ለመቅሰም ሞክሯል፡፡ ችግሩንም ሊፈታ የሚችል የግል ትምህርት ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥና ክፍያ ሥርዓት መመሪያ ወጥቷል›› ብለዋል፡፡

ከሐምሌ 2011 ዓ.ም ጀምሮም መመሪያው ተግባራዊ እንዲሆን መወሰኑን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡ መመሪያው የተማሪዎችን አቅም ያገናዘበ ትምህርት እንዲሰጥ ያዝዛል፣ እንደ ቋንቋ ያሉና ሌሎች ተጨማሪ የትምህርት ዓይነቶችን እንሰጣለን በሚል ከመደበኛ ከፍለ ጊዜ መቀነስንም ይከለክላል፤ ተጨማሪ የማካካሻ (አጋዥ) የትምህርት ዓይነቶችን እንሰጣለን በሚል ከወላጆች ጋር ያለውይይትና ያለስምምነት የሚተገበር የክፍያ ጭማሪ አግባብ አለመሆኑንም ያስቀምጣል፡፡ መመሪያው ለሁሉም የሚመለከታቸው አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች እስከ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት መላኩን፤ የግል ትምህርት ቤቶች የሚሰጡትን አገልግሎትና ክፍያ ተመጣጣኝ ያደርገዋል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ተናግረዋል፡፡

‹‹ክፍያውን ከዚህ በላይ አትጨምሩም ብሎ ለመገደብ በነፃ ገበያ ሥርዓቱና በስልጣን ምክንያት እንቸገራለን›› ያሉት አቶ አንማው ስልጣኑ የትምህርት ሕግ የሚያወጣው የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአገልግሎትና በክፍያ ዙሪያ ለምክክር ሲጠራ ወላጅ ተገኝቶ ሐሳቡን በመግለፅ መታገል እንደሚገባው ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ ማንኛውም ትምህርት ቤት ሥርዓተ ትምህርቱን መሠረት አድርጎ፣ ተማሪዎቹ የሚያገኙትን አገልግሎት ወላጆች አውቀው የሚሰጥ እንዲሆን በመመሪያ እንደተቀመጠ ተናግረዋል፡፡ የስድስት ወር ክፍያ አንድ ጊዜ የሚጠየቅበት አሠራር ያላቸው ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ድርጊቱ ተገቢ ባለመሆኑ ትምህርት ቤቶቹ ከዚህ እንዲታቀቡ በመመሪያው መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡

‹‹በቀጣዩ ዓመት ተጨማሪ ግንባታ አደርጋለሁ›› በሚልና ሌላም መሠል ምክንያት በአንድ ጊዜ የሦስት ወይም የስድስት ወር ክፍያ መጠየቅና ማስገደድ እንደማይቻል ታውቋል፡፡ አንድ የግል ትምህርት ቤት ክፍያ እጨምራለሁ ካለ የተማሪ ወላጆች (አሳዳጊዎች) ከ50 በመቶ በላይ መገኘታቸውን ማረጋገጥና ቃለ-ጉባኤ መያዝ፣ በጭምሪው ላይ መግባባት ከተቻለ በኋላ አጠቃላይ መረጃው ለትምህርት ጽሕፈት ቤት ወይም ቢሮ ቀርቦ ተቀባይነት ካገኘ ጭማሪው እንደሚጸድቅም በመመሪያው መቀመጡም ታውቋል፡፡ ‹‹ረጅም ዕድሜ ባስቆጠሩ ግብዓቶች የክፍያ ጭማሪ የሚያደርጉ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ፤ አገልግሎቱና ከፍያው ተመጣጣኝ ቀርቶ ተቀራራቢ አይደለም፤ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ትርፍ ለማጋበስ የተቋቋሙ እንዳልሆኑ ይገልጻሉ፤ ገቢያቸውም ተመልሶ ለማኅበረሰቡ የሚውል እንደሆነ ቢገልጹም ጭማሪ ክፍያ አድርገው ገንዘቡ የት እንደገባ ለማወቅ የተቸገርንባቸውን አግኝተናል›› ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ቅድመ መደበኛ 403፣ ሁለተኛ ደረጃ 21፣ መጀመሪያ ደረጃ 117 የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

Image