<> Skip to main content
Submitted by admin on Fri, 01/12/2018 - 19:59

ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ የምትሳተፍባቸውን የስፖርት ዓይነቶች ለማሳደግ  ጥረት እያደረጉ መሆኑን የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ገለጹ።

 ኢትዮጵያ ... 1956 በአውስትራሊያ ሜልቦርን በተካሄደው ኦሎምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች እየተሳተፈች ነበር።

 ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በቦክስ፣ በውሃ ዋናና ብስክሌት ተሰትፋ ነበረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በኦሎምፒክ ስፖርቶች የሚደረገው ተሳትፎ እየተቀዛቀዘ መጥቷል።

 አገሪቷ በኦሎምፒክ  የምትሳተፍባቸውን  የስፖርት ዓይነቶች በማሳደግ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን  አስመልክቶ የስፖርት ፌዴሬሽኖች አመራር አባላትን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር አነጋግሯል።

 የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው መኮንን፤ ከሁለት ዓመት በኋላ በጃፓን በሚካሄደው 28ኛው ቶኪዮ ኦሎምፒክ  በብስክሌት ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ስፖርተኞችን ለማሳተፍ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።

 ባለፉት ስድስት ወራት ብስክሌተኞችና አሰልጣኞች ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ ሄደው ዓለም ዓቀፍ ስልጠና እንዲያገኙና ብቃታቸውን እንዲያጎለብቱ መደረጉን ገልጸው፤ በቀጣይ መሰል ስልጠናዎች እንደሚዘጋጁም ጠቁመዋል።

 44 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የብስክሌት ተወዳዳሪው ጽጋቡ ገብረማርያም  ማጣሪያውን በማለፍ ... 2016 በተካሄደው የሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ መሳተፉን አስታውሰዋል።

 ስፖርቱ ዘላቂነት ባለው መልኩ ተሳትፎ ለማድረግና ውጤታማ ለመሆን ፌዴሬሽኑ እየሰራ መሆኑን ነው አቶ ግዛቸው ያብራሩት።

 የኢትዮጵያ የቦክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ማዳ በበኩላቸው፤ ...1964 በቶኪዮ ኦሎምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎ የተደረገበትን የቦክስ ስፖርት ዳግም ወደ ኦሎምፒክ ውድድር ለመመለስ "ቦክሰኞች በዓለም አቀፍ ማጣሪያ ውድድሮች እንዲሳተፉ የዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው" ብለዋል።

 ከመጋቢት 2010 .. ጀምሮ በሚካሄዱ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድሮች ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

 በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ የሚያስችለውና 2011 .. በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በሚካሄደው የዓለም የቦክስ ውድድር ሻምፒዮና ብቁ ቦክሰኞች እንዲሳተፉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

 ብቁ የሆኑ አትሌቶችን ለማፍራት በታዳጊዎችና አዋቂዎች ዘርፍ የቦክስ ውድድሮች በአገር ውስጥ እንደሚካሄድም አመልክተዋል።

 የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በሪዮ ኦሎምፒክ ማግስት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የካራቴ ስፖርት ከቀጣዩ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ጀምሮ እንዲካተት በመወሰኑ ኢትዮጵያም በስፖርቱ እንድትሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ካራቴ ፌዴሬሽን አቶ አሰፋ አንጄሎ ገልጸዋል።

 የታዳጊ ፕሮጀክትና አገር አቀፍ የቦክስ ውድድሮች የሚገኙ ተወዳዳሪዎች በመመልመል በአህጉራዊና የዓለም አቀፉ የካራቴ ፌዴሬሽን እውቅና በሰጣቸው ውድድሮች እንዲሳተፉ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

 ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ የምትሳተፍባቸውን ስፖርቶች ለማሳደግ ፌዴሬሽኖቹ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ባለድርሻ አካላት እንዲደግፏቸው  ጠይቀዋል።

 የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ አቶ ታምራት በቀለ እንዳሉት፤ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በስምንት ስፖርቶች ለመሳተፍ በእቅድ ተይዟል።

 ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ያስመዘገበችው ውጤትና በስፖርቶቹ ለመሳተፍ የሚያስችሉ በቂ የማጣሪያ ውድድሮች በመኖራቸው "በአትሌቲክስ፣ ውሃ ዋና፣ ብስክሌት፣ እግር ኳስ፣ ቦክስ፣ ቴኳንዶ፣ ጁዶና ኢላማ ተኩስ አገሪቷ በቀጣዩ ኦሎምፒክ ልትሳተፍባቸው ያቀደቻቸው የስፖርት ዓይነቶች ናቸው" ብለዋል።

 በአልጄሪያ ርዕሰ መዲና አልጀርስ የሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ፣ በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ የሚካሄደው ሶስተኛው የወጣቶች ኦሎምፒክና በጊኒ ቢሳው የሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በኦሎምፒክ ለመሳተፍ የሚያስችል የማጣሪያ ውድድሮች እንደሚገኙባቸው ነው አቶ ታምራት ያብራሩት።

 ከአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተጨማሪ በመጋቢት 2010 .. በትግራይ መቀሌ ከተማ በሚካሄደው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ውድድር ብቁ የሆኑ ስፖርተኞችን ለማግኘት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

 ኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ስፖርት ፌዴሬሽኖች እቅዱን ለማሳካት የሶስትዮሽ ጥምረት በመመስረት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 ስፖርት ፌዴሬሽኖቹ ያላቸውን ዓቅም እንዲያጎለብቱ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ የቁሳቁስ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አቶ ታምራት አብራርተዋል።

Image