<> Skip to main content
ለተፈናቃዮች ከ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ፡፡

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተፈናቃዮች ከ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ፡፡

Image may contain: 5 people, people sitting and indoor

ባሕር ዳር፡ የካቲት 01/2011ዓ.ም (አብመድ) ከአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የተውጣጡ ነዋሪዎች፣ የወጣት ማኅበራት፣ የሴቶች ማኅበር እና አመራሮች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አድርገዋል፡፡

3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ እህል እና የተለያዩ እርዳታዎችን ለክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስረክበዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ውቤ ነጋሽ ድጋፉን ለማድረስ ወደ ባሕር ዳር ከመጡት መካከል አንዱ ናቸው፡፡

በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም ራያ እና አላማጣ አካባቢ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው የተሰደዱ ወገኖችን ከተጠለሉበት ሥፍራ ተመልክተዋል፡፡ ለጊዚያዊ ችግራቸው እንዲሆን በማሰብም 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ጤፍ ፣ስንዴ ፣ስኳር፣ ማካሮኒ ፣ፍራሽ እና ብርድ ልብስ ድጋፍ መደረጉንም ነግረውናል፡፡ እኛም ከሥፍራው ተገኝተን ተመልክተናል፡፡

ሌላዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ በፈቃዱ ነፍሰጡር እናቶች፣ህፃናት እና ጨቅላ ህጻናትን የያዙ እናቶች ተፈናቅለው በማየታቸው ወገኖቻቸውን ለማገዝ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ድጋፉ በዚህ እንደማይቆም እና መንግሥት ደግሞ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በትኩረት እንዲሰራም አስተያዬት ሰጥተዋል፡፡

የአማራ ክልል የአደጋ መከላከል እና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እያሱ መስፍን የአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ያደረጉትን ድጋፍ ለተፈናቃዮች በተገቢው እንደሚያደርሱ ተናግረዋል፡፡ እስከአሁን ባለው ጊዜ ከአዲስ አበባ ህዝብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መገኘቱንም ነው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡-አዳሙ ሽባባው

Image
The website encountered an unexpected error. Please try again later.