<> Skip to main content
የተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ክልሎችን ገቢ እያሳጣ ነው፡፡

የተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ክልሎችን ገቢ እያሳጣ ነው፡፡

ባሕር ዳር፡ የካቲት 28/2011 ዓ.ም (አብመድ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሎች የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ክልሎችን የሚገልጹ መለያ ኮዶችን እየተጠቀሙ አይደለም፡፡ በተለይ በአማራ ክልል የኮድ 2 እና 3 ተሽከርካሪዎች ሰሌዳዎች በአብዛኛው ‹‹አአ›› እና ‹‹ኢት›› እየሆኑ ነው፡፡ ከክልሎች ይልቅ ‹‹አአ›› እና ‹‹ኢት›› የሚሉ መለያ ኮዶችን እየተጠቀሙ ነው፤ ለዚህ ባለቤቶቹ የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ በሀገሪቱ እየታዬ ያለው የደኅንነት ዋስትና አሳሰቢ መሆኑን ነው፡፡ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አሽከርካሪዎችም የአንድን ክልል ነዋሪነት የሚገልጽ ሰሌዳ ቁጥር አድርጎ መንቀሳቀስ ለጥቃት እያጋለጠ በመሆኑ ያለስጋት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ለመንቀሳቀስ አዲስ አበባ ወይም ኢትዮጵያ የሚል መለያ ያለው ሰሌዳ እንደ አማራጭ እንደሚጠቀሙ ነው የነገሩን፡፡

No photo description available.

በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው ብሔር ተኮር ጥቃት የአንድን ክልል የሰሌዳ ቁጥር ይዞ በመላ ሀገሪቱ መንቀሳሰቀስን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ የክልል ስም የሚገልጽ ሰሌዳ ያላቸው ተሸከርካሪዎች ከራሳቸው ክልል ወጥተው ወደ ሌሎች ክልል ሲንቀሳቀሱ ፍተሻው የክልሉን ወሰን እንደተሻገሩ ይጀምራል፡፡ ተሽከርካሪውም የሌላ ሀገር ሰሌዳ ያለው ተደርጎ እንደሚቆጠር አሽከርካሪዎች ነግረውናል፡፡ ይህ ደግሞ ዜጎች በመላ ሀገሪቱ በነጻነት ተዘዋውረው እንዳይሰሩ እና እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት እየተራራቀ እንዲሄድ የሚያደርግ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር ወይዘሮ አሚነት ጀማል የተሸከርካሪ ሰሌዳ ቁጥር አሰጣጥ እንዳጠቃላይ ሲታይ አንዱን ክልል ከአንዱ ክልል ጋር አብሮ እንዳይሰራ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርከሪዎች ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ተሻግረው እንዳይሰሩ መደረጉ ሌሎች ተሸከርካሪዎች በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ ለመደረጉ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

No photo description available.

ወይዘሮ አሚነት ‹‹በሀገሪቱ የጸደቀው የተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥር አሰጣጥ ክልሎችን የሚያራርቅ ነው፡፡ ችግሩ እንዲታረም ለሚመለከተው አካል ጥያቄ እናቀርባለን›› ብለዋል፡፡


‹‹ኢት›› እና ‹‹አአ›› ሰሌዳ መለያቸው የሆነ ተሸከርካሪዎች በአማራ ክልል ተበራክተዋል፤ ዓመታዊ መዋጮ እና ግብር ደግሞ ከክልሉ ውጭ አዲስ አበባ ሄደው ይከፍላሉ፡፡ በክልሎች የትራፊክ መጨናነቅ እየፈጠሩ፣ ብክለት እያስከተሉና ክልሎች የሚገነቧቸውን መንገዶችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች እየተጠቀሙ ግብርና የልዩ ልዩ አገልግሎት ክፍያዎችን ግን ወደ አዲስ አበባ ሄደው ይፈጽማሉ፡፡

No photo description available.
ከወይዘሮ አሚነት ባገኘነው መረጃ መሠረት አአ እና ኢት የሚል ሰሌዳ ይዘው በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለክልሉ ምንም የሚያበረክቱት ገቢ የለም፡፡ ነገር ግን ክልሉ ከፌዴራል ውክልና ተቀብሎ ‹ኢት› የሚል መለያ ያለው ሰሌዳ እየሰጠ ነው፡፡ ‹አአ› የሚል መለያ ሰሌዳ ያላቸው ተሽከርካሪዎች ግን ከክልሉ ምንም አገልግሎት እንደማያገኙና የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲፈልጉ ባለሀብቶቹ አዲስ አበባ ለመሄድ እንደሚገደዱ ነው የሰማነው፡፡

መለያ ሰሌዳቸው ክልሉን የማይገልጹ በክልሉ ያሉ ተሸከርካሪዎች ዓመታዊ ክፍያ እና ግብርም ለአዲስ አበባ ወይንም ለፌደራል መንገድ ትራንስፖርት እንደሚከፍሉ ወይዘሮ አሚነት ነግረውናል፡፡ ይህም ክልሉ ሊያገኝ የሚገባውን የተሸከርካሪ ገቢ እንዳያገኝ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ 

No photo description available.


በሀገሪቱ እየታየ የመጣው የሰላም እጦት ተሽከርካሪዎች አአ እና ኢት የሚሉ ሰሌዳዎችን እንዲያወጡ ማስገደዱ ቢታመንም መኪኖቹ ከውጭ የሚገቡ ስለሆነ አስፈላጊ ሂደቶችን አዲስ አበባ ጨርሰው ወደ ክልሎች የሚገቡበት ሁኔታ መኖርም ሌላው ምክንያት እንደሆነ ወይዘሮ አሚነት አስገንዝበዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ክልሉን ገቢ ከማሳጣት አልፎ ተጠቃሚዎች በዕድሳት እና በተለያዩ ግልጋሎቶች እንዲቸገሩ አድርጓል፡፡ የአማራ ክልል ሰሌዳ ከሚያወጡ ተሸከርካሪዎች እና ከተለያዩ ክፍያዎች በዓመት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

No photo description available.

ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የነበረው የተሽከርካሪ ሰሌዳ አሰጣጥ ከተሞችን መሠረት ያደረገ ‹‹ጎን፣ ደማ፣ አአ፣ ነቀ፣ መቀ …›› የሚል ነበር፡፡ ከ1990ዎቹ አጋማሽ በኋላ ግን የተሽከርካሪዎች ሰሌዳ በከተሞች መሆኑ ቀርቶ በዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች ስም አኅጽሮተ ቃል እና ለረዥም ርቀት ተሽከርካሪዎች ኢት እንዲሆን ተደርጓል፤ የዲፕሎማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ደግሞ ‹‹ኮዲ›› እና ‹‹ዕድ›› የሚሉ መለያዎችን እንዲጠቀሙ ተደርጓል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረትን የመሠሉ ዓለማቀፍ ተቋማት ደግሞ የራሳቸው መለያ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ ይህንንም አንዳንዶች ‹‹የአንድ ኩባንያ ምርት የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ብሔር እየሰጡ መከፋፈል ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የከፋ ነው›› በማለት እየተቹት ነው፡፡

 

ዘጋቢ፡-ታርቆ ክንዴ

Image