<> Skip to main content
ክስ መመሥረት በሚያስችለን ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዐቃቢ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጧቸው ማብራሪያዎች፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 04/2011ዓ.ም (አብመድ) በተቻለ መጠን ተጠርጣሪዎቹን ጉዳያቸውን አጣርተናል፤ በአብዛኛው የሰው ምስክርም ተቀብለናል፤ የሰነድ ማስረጃዎችንም አሰባስበናል፡፡ ክስ መመሥረት በሚያስችለን ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡

በቀጣይም ትላልቅ በምርመራ ሂደት ላይ ያሉ አሉ፡፡ ከግዥ ቀጥሎ በግንባታና ብድር በመሳሰሉት ዙሪያ ምርመራውን ጀምረናል፤ ግን ሰፊ ጊዜ የሚወስዱ ናቸው፡፡

ሥራችን የሚያስቀጣና የተዘረፈውን የመንግሥት ሀብትና ንብረት የሚያስመልስ መሆን አለበት፡፡

አንዳንዶቹ የመንግሥትን ሀብት በውጭም ኢንቨስት ያደረጉ አሉ፤ በዚህ ዙሪያ ከሀገራቱ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡

Image may contain: 1 person

በሀገር ውስጥም በዓለማቀፍም የተመዘበሩ የመንግሥት ሀብቶችን የማስመለስ ሥራ የሚሠራ አካልም አልነበረም፡፡ አሁን ሥራ ጀምረናል መንግሥትም ቁርጠኛ ነው፡፡
ሥራው የዘመቻም አይደለም፤ የተከማቸ ጉዳይን የማጥራት ሁኔታም አይደለም፡፡ የግድ የተፈጸሙ ድርጊቶችን ማጥራት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ የተሠራው ሕግን ተከትሎ የመንግሥትና ሕዝብን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ የተሠራ ነው፡፡

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚሠራም ነው፤ በተለይ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ሆነን እየሠራን ነው፡፡

ሕገ-ወጥነትን በተመለከተም መንግሥት በሕገ-መንግሥት የተቀመጡ መብቶችን ሕዝብ እንዲጠቀም ፈቅዷል፤ ይህ ማለት ግን ሕግን እንዲተላለፉ መፍቀድ አይደለም፡፡ ስለሆነም በዋናነት የሴራዎች ጠንሳሽ ሆነው ከሚሠሩት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ እንሠራለን፡፡ ሕግ ማስከበር ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በግጭት፣ መንገድ በመዝጋት … መንግሥትን ለመተካት የሚደረጉ ሂደቶችን በተመለከተ ሕግ ለማስከበር ይሠራል፡፡ ነገር ግን በቅስቀሳ ተመሥርቶ አይሠራም፡፡

Image may contain: 8 people, people sitting and indoor

የፖለቲካ አስሳሰቡን በማራመዱ ብቻ ግን የምንከስስበት ሂደት የለም፡፡ ሕገ-ወጥነትና ሕጋዊ ነገር ቀላቅሎ የሚሄዱት ላይ ግን እርምጃ እንወስዳለን፡፡ የጥላቻና የሀሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩትን በተመለከተ ከዓለማቀፍ ድርጅቶችም ጋር እየሠራን ነው፤ ሕጉ እንደጸደቀ ወደ ሥራ እንገባለን፡፡

ጤፍን በተመለከተ ሥራው የቆዬ ነው፡፡ የጥናት ሥራው ተጠናቅቆ ክስ ለመመስረት በሚቻልበት ደረጃ ነው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር እንገባለን፡፡

በሰብዓዊ መብት የተጠረጠሩና በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ አሉ፤ ግን ዕቅድ አውጥተን እየሠራን ነው፡፡ የተወሰኑት በሀገር ውስጥ ተደብቀዋል፤ የተወሰኑት በውጭ ሀገር ይገኛሉ፡፡ ለማቅረብ እየሠራን ነው፤ ይህም ሳይሆን ግን በሌሉበት ክስ መመሥረት የምንችልበት የሕግ አግባብ አለ፡፡ ይህ መሆኑ የሚጎዳው ራሱን ተጠርጣሪውን ነው፡፡

የሽብር ጥቃቱን በተመለከተ ምርመራው ገና አላለቀም፤ ገና ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችም አሉ፡፡ ሽብሩን ያዘጋጀው አልሸባብ ነው፤ ግን ገና ያላለቀ ጉዳይ ነው፡፡

በቻይና የተያዘችውን ልጅ በተመለከተ እርሷን ስለሚጎዳ መረጃ መስጠት አይገባም፡፡ የምናደርገውን ነገር እያደረግን ነው፤ መገናኛ ብዙኃን ባይዘግቡት ጥሩ ነው፡፡

ማረሚያ ቤትን በተመለከተ ባደረግነው ጉብኝት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የለም፤ በፖሊስ ጣብያም ጭምር የለም፡፡ ከዚህ በፊት ችግር ፈጥረዋል የተባሉትን ለሕግ አቅርበናል፡፡ ከዚያ ውጭ የነበረው ሁሉ ጥፋተኛ ነው ማለት ትክክል አይደለም፡፡ በማረሚያ ቤትም ሆነ በማቆያ ቤት ያሉና የሰብዓዊ መብት የሚጥሱ የሉም፡፡

ግጭቶች የሚፈጠርበትን ምክንያት በተመለከተ በአብዛኛው አካባቢ የመንግሥት አስተዳደር እርከን እንዲፈጠር የሚፈጠሩ ግጭቶች አሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም ራሳቸው የመንግሥት ባለስልጣናት እጃቸው እንዳለበት ይታወቃል፤ በዝርዝር እየሠራንበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ጠንሳሾችን የመለየትና ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየሠራን ነው፡፡

Image may contain: 8 people, people sitting

በተቋማት ላይ ምዝበራ ሲፈጸም የሕግ ችግር አይደለም፤ የሕግ ጥሰት ተፈጽሞ የተሠራ ነው፡፡ ለዚህም ነው ወንጀል የሆነው፡፡ ክፍተቱ ሕጉን በመተላለፍ የተፈጸመ ነው፡፡

ከሰብዓዊ መብት ጥሰት አንጻር በተለይ በፌዴራል ደረጃ ባለው አካል እንደ በፊቱ የሚፈጸምና ሪፖርት የተደረገልን የለም፡፡ የክልሎችን ጉዳይ ወርደን አላየንም፡፡

መብቶች ሲፈቀዱ መብትና ግዴታን አውቆ የሚንቀሳቀስ ዜጋ አለመኖር ካልሆነ በቀር በፓርቲዎች ደረጃ ችግር ስለመኖሩ አልተገመገመም፡፡ እኛ ሕጉን መሠረት አድርገን እያዬን ነው፡፡ የፖሊስ ኃይሉ ተዳክሟል የሚለውም ተገቢ አይደለም፤ የነገርኳችሁ ሁሉ የተሠራው በዚሁ ኃይል ነው፡፡ ችግሮች ግን አይኖሩም አይባሉም፡፡ ፖሊስ ሕይወቱን ጭምር እየሠዋ እየሠራ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም ሊያግዘው ይገባል፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

Image