<> Skip to main content
‹‹ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ገብቶናል፡፡›› የሰሜን ጎንደር ዞ

‹‹ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ገብቶናል፡፡›› የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ

‹‹ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እሳቱ አሁን ከአቅም በላይ ነው፤ ይመጣል የተባለው አውሮፕላን መቼ እንደሚመጣም ማወቅ አልቻልንም፡፡›› የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2011ዓ.ም (አብመድ) የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎ ወደ ቆላማው ክፍል ወርዷል፤ ‹አግዳሚያ› ወደሚባለው አካባቢ ከዞረ የሚያስከትለው ውድመት የከፋ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

Image may contain: cloud, sky, mountain, outdoor and nature

ስድስተኛ ቀኑን በያዘው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎ በደጋማው ክፍል ግጭ አካባቢ ያለውን ማጥፋት ተችሏል፡፡ ነገር ግን በገደላማው የፓርኩ ክፍል የገባው እሳት በሙጭላ አካባቢ ከፍተኛ ነበልባል እየፈጠረና እየተስፋፋ መሆኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ለምለሙ ለአብመድ ዛሬ ረፋድ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በሰው ኃይል ለመቆጣጠር ያለንን አቅም ሁሉ አሟጥጠን ተጠቅመናል፤ የደጋማውን ክፍል መቆጣጠር ችለናል፡፡ ነገር ግን ወደገደሉ ክፍል በሙጭላ በኩል የገባው እሳት በሰው አቅም የምንቆጣጠረው አይደለም፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ እየነደደ ነው፡፡ አሁን ካለበት አልፎ ወደ አግዳሚያ በኩል ከዞረ ደግሞ አደጋው እጅግ አስከፊ ይሆናል፤ ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ገብቶናል›› ነው ያሉት፡፡

‹‹ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እሳቱ አሁን ከአቅም በላይ ነው፤ ይመጣል የተባለው አውሮፕላን መቼ እንደሚመጣም ማወቅ አልቻልንም›› ያሉት ደግሞ የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣና ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ ናቸው፡፡

Image may contain: cloud, sky, mountain, outdoor and nature

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ስለአውሮፕላኖች መምጣጥ አለመምጣት በቂ መረጃ እንደሌላውና ነገር ግን ሁኔታውን ተመልክቶ መግለጫ ለመስጠት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችንና ጋዜጠኞችን ይዞ ወደ ፓርኩ እያመራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ትናንት በቦታው ተገኝተው የእሳት ቃጠለው ያለበትን ሁኔታ ጎብኝተው ነበር፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያው በቃጠሎው አካባቢ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ መጣሉን ትናንት ማምሻውን ዘግበው ነበር፤ ነገር ግን ዝናብ አለመጣሉን የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪና ሌሎችም በቦታው የሚገኙ ምንጮች አረጋግጠውልናል፡፡ ‹‹ቃጠሎ በሌለበት የፓርኩ ክፍል መጠነኛ ካፊያ ጀምሮ ነበር፤ ከዚያ ውጭ እሳቱን ሊያጠፋ የሚችልና ወደዚያው አካባቢ የጣለ በረዶ ቀርቶ መጠነኛ ካፊያም አልነበረም›› ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

Image