<> Skip to main content
የባለሙያዎች ቡድኑ ተጨማሪ ድጋፍ በምን መልኩ እንደሚደረግ የሚያሳውቅ ነው፡፡

የእስራኤል የእሳት ተቆጣጣሪ የባለሙያዎች ቡድንና አንድ የኬንያ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ጎንደር ገብተዋል፤ ሄሊኮፕተሯም ወደ ስሜን ፓርክ አቅንታለች፡፡

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 06/2011ዓ.ም (አብመድ) በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ዛሬ ረፋድ ለአብመድ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያና የእስራኤል መንግሥታት ትብብር የባለሙያዎቹ ቡድኑ ተልኳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሆ በጉዳዩ ዙሪያ ባለፈው ዓርብ በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ነው የባለሙያዎቹ ቡድን የተላከው፡፡

የባለሙያዎች ቡድኑ ከእስራኤል የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል አገልግሎት የተውጣጣ 10 አባላት ያሉት ሆኖ አንደኛው የቡድኑ ሐኪም ቀሪዎቹ ግን የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

 

Image may contain: 1 person, smiling, beard
ቡድኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሆ ትዕዛዝ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንቅስቃሴውን እንደሚያስተባብሩት መግለጫው ያሳያል፡፡

 

ቡድኑ ጎንደር ሲገባ የተቀበሉት የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ የክልሉ መንግሥት ለባለሙያዎች ቡድኑ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ መጠበቁን ገልጸዋል፡፡

የባለሙያዎች ቡድኑ የእሳት ቃጠሎውን ሁኔታና አጠቃላይ መልክአ ምድሩን የተመለከቱ ሀቆችን በመመልከት ተጨማሪ ድጋፍ በምን መልኩ እንደሚደረግ የሚያሳውቅ ነው፡፡

 

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም የባለሙያዎች ቡድን የእሳቱን ሁኔታ ተመልክቶ የሚሰጠውን ምክር ሐሳብ በፍጥነት ለመተግበር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

Image may contain: 1 person, standing and outdoor

ከ1ሺህ 200 እስከ 1ሺህ 300 ሊትር ውኃ መሸከምና መርጨት የሚችል የኬንያ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተርም ጎንደር መግባቱን ዶክተር በላይነህ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ ሄሊኮፕተሩ ውኃ የሚቀዳበት ቦታም መለዬቱም ታውቋል፡፡ ሄሊኮፕተሯ ከደቂቃዎች በፊት ወደ ፓርኩ አቅንታለች፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ - ከጎንደር

Image