<> ሀሳቤ | Amhara Mass Media Agency Skip to main content
 • ሀሳብ

  ለኢትዮጵያ ኖሩ፣ ለኢትዮጵም ሞቱ፤ ጀግናው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ኢንጂኒየር ስመኘው በቀለ፡፡

  ብዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በባለሙያነት እና በኃላፊነት አስተዳድረዋል፤ለውጤትም አብቅተዋል፡፡ ከ2003 ዓ.ም ህይዎቱ እስካለፈችበት ሐምሌ 19/ 2010ዓ.ም ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ራሳቸውን እያቀለጡ በሚሊዮኖች ለምንቆጠር ኢትዮጵያዊያን ብርሃን መሆንን ህይዎታቸው አድርገውታልና በጉባ በረሃ ኑሯቸውን ካደረጉ ሰባት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

  የጉባ በረሃ የዓየር ጸባይ ለዓመታት በዛው እየኖሩ ሌት ከቀን ለመስራት አይደለም ጎብኝቶ ለመመለስ ፈታኝ ነው፡፡ ኢንጂኒየር ስመኘው ግን ከሌሎች ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ጋር ሆነው ግን ደግሞ የህዝብን ከድህነት የመውጣት ታላቅ አደራበ በፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነት ተሸክመው ነበር ስራውን በበላይነት እየመሩ የነበሩት፡፡ ግድቡ የሚገነባበት ስፍራ ዓየሩ እንደ እሳት ይጋረፋል፡፡ ኢንጂኒየር ስመኘው ግን ራሳቸውን ለሃገር እና ለህዝብ አደራ አሳልፈው ሰጡ፡፡ ለ ሰባት ዓመታትም ከሞቀ ቤታቸው፣ ከትዳር እና ከልጆቻቸው ርቀው፣ ምቾትን ሳይሆን ጨለማን በብርሃን ድል መንሳትን አስቀድመው ኑሯቸውን ጉባ በረሃ ውስጥ አደረጉ፡፡ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጀግና ልጅነታቸውንም በተግባር አሳዩ፡፡

  ዳሩ ምን ያደርጋል እንደልጆቻቸው የሚሰስቱለትን፣ መልክ እና ውበታቸውን ያጠፉበትን፣ በበረሃ እና በአስቸጋሪ ኑሮ የተፈተኑበትን የኢትዮጵያዊያን የብርሃን ተስፋ ግድብ ዕውን መሆን ሳያዩ በገዳዮች ነፍሳቸውን ተቀሙ፡፡ በድንገት እንደወጡም የሞት መርዷቸው ተሰማ፡፡ ኢንጂኒየር ስመኘው ሙያ እና ህይዎታቸውን ለኢትዮጵያ የሰጡ፤ ለህዝብ ብርሃን ለመሆን የተሰው ውድ የሃገር ልጅ፡፡ ኢትዮጵያም የሐዘን ማቅ ለበሰች፤የደም እምባም አነባች፡፡ ያጣችው የሚሊዮኖችን አደራ ተሸክሞ ለሚሊዮኖች ብርሃን ለመሆን ራሱን ያቀለጠላትን፣ ራሱን ለመስዋዕትነት ያቀረበላትን ጀግና ልጇን ነውና፡፡

  አሁን ኢትዮጵያዊያኑ አንድ ብርቱ ጥያወቄ እያሰሙ ነው፡፡ ገዳዮች በቶሎ ታውቀው ለፍርድ እንዲቀርቡ፡፡ እኔም አልኩ እንደዚህ የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴን ግጥም ተዋስሁና፣ ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡ ምንኛ ባለርዕይነት፣ ምንኛ ባለብሩህ አዕምሮነት ይሆን የሃገርን እውነታ ዘመንን አሻግሮ እንዲህ ባማሩ ቁጥብ ስንኞች መግለጽ መቻል? እስኪ እናንተው ፍረዱት የኢትዮጵያ ልጆች፣ ኢትዮጵያ ለማን? ለሞተላት፣ ትዳር፣ ልጅ፣ቤት፣ ምቾት….ሳይል ለሃገር፣ ለኢትዮጵያ ለኖረ ጀግዋና ወይስ ለገዳይዋ? እኛም ነፍስ ይማር ብለናል፡፡

  ከ እውነት አሸናፊ