ለኢትዮጵያ ወደ ሌላ ሀገራት መውጫ በር በመሆናቸው ለጎረቤት ሀገራት ደኅንነት ትኩረት እንደሚሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ፡፡

0
35

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ፈጥረው በንግድ መተሳሰር ካልቻሉ ሌላውን ጉዳይ ማስኬድ እንደማይቻላቸው ዶክተር ዐብይ አሕመድ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ‘ሀገሪቱ ለውጭ ጉዳይ የምትሰጠውን ትኩረት ያህል ለውስጥ ጉዳይ እየሰጠች አይደለም’ ተብሎ ዛሬ ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው፡፡ በምላሻቸውም ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት ከምትሰጠው ትኩረት ባለፈ ለጎረቤት ሀገሮች ቅድሚያ የምትሰጠው በጎረቤት ሀገራት ሰላም የውስጥ ብሄራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ ስለሚቻል ነው ብለዋል፡፡
ጎረቤት ሀገራት ጎረቤት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያንም የሚኖሩባቸው በመሆኑ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ትኩረት መስጠቱ ተገቢ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

“በጎረቤት ሀገራት የሚፈጠር ችግር ሀገሪቱን በቀጥታ ይጎዳል፤ ከጎረቤት ሀገራትም ውጭ ቢሆን እንደዚሁ ነው፤ ባለፈው ጊዜ በሳዑዲ የነዳጅ ማውጫ ላይ የተፈጠረው ችግር የነዳጅ ዋጋው እንዲንር ምክንያት ነበር፤ ይህም ሀገሪቱን ጎድቷል፤ በመሆኑም ሀገራት ላይ የሚፈጠረው ችግር ለሀገሪቱ ተጽዕኖ እንዳለው መገንዘብ ተገቢ ነው” ብለዋል ዶክተር ዐብይ፡፡ ለጎረቤት ሀገራት ትኩረት ሰጥቶ መስራት የሀገርን ደኅንነት ማረጋገጥ እንደሚያስችል፣ የውስጥ እና የውጭ ጉዳይም በተናጠል የሚታይ ሳይሆን ብዙ ቦታ ላይ የሚተሳሰር እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

“ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዥዎች ካሰመሩት ሰው ሰራሽ ድንበር ባለፈ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በዘር፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት እና በብዙ ነገሮች አንድ ቤተሰብ ሕዝቦች ናቸው፤ የኢኮኖሚ ትስስር ይፈጠር እየተባለ ያለውም አንድ ቤተሰብ ስለሆንን ነው” ብለዋል፡፡
የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ፈጥረው በንግድ መተሳሰር ካልቻሉ ሌላውን ጉዳይ ማስኬድ እንደማይቻላቸውም ነው ለምክር ቤት አባላቱ ያስረዱት፡፡

በሀገር ውስጥ የሰላም ሚኒስቴር የተቋቋመው ከምንም በላይ የሰላም ጉዳይ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ለሰላም ትኩረት በመሰጠቱ ለበርካታ ዓመታት ተራርቀው የኖሩ የሀይማኖት ተቋማት እርቅ እንዲፈጥሩ ተደርጓል፤ የተፈናቀሉትም በአብዛኛው ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ ቪዛ የማይፈቀድላቸው በውጭ የሚኖሩ ከ45 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ መፈቀዱም ለሀገር ሰላም ትኩረት በመሰጠቱ እንደሆነ መዘንጋት እንደሌለበት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ በርካታ እስረኞች በሀገር ውስጥም በውጭም እንዲፈቱ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡

“የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ ሲባል መስዋዕት የሚሆኑ አካላትን ዋጋ ክብር ልንሰጥ ይገባል ያሉት ዶክተር ዐብይ የምንታገሰው የለመድነው ቀላሉ መንገድ ማሰር እና መምታት ስለሆነ ትንሽም ቢሆን ታግስን እንለፍ በሚል ነው” ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here