‹‹ልክ እንደ ዶክተር አያና ደግነትን ከሌሎች ሰዎች ሳይጠብቁ የመልካምነት ሐዋርያ ሆኖ መገኘት ለሆነለት መታደል ነው፡፡›› የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች

0
66

“ሕዝቡ አመሥጋኝ ስለሆነ እንጅ ብዙ አልሠራሁም፡፡” ዶክተር አያና ስማቸው
ወጣት ናቸው፤ በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥም ይገኛሉ። በየዕለታዊ እንቅስቃሴያቸው በሚያከናውኗቸው ማኅበራዊ ተግባራት ማኅበራዊ ተቀባይነታቸው ከፍ ያለ እንደሆነም ይነገራል፤ ዶክተር አያና ስማቸው። ዶክተር አያና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳድር እንጅባራ ከተማ ዕውቅ የጥርስ ሐኪም ናቸው። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩትም በአንክሻ ወረዳ ነው።
የሕክምና ትምህርታቸውን በጂማ ዩኒቨርሲቲ ተምረውም በአዲስ አበባ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል በሙያቸው ለአንድ ዓመት ያክል አገልግለዋል። ‹‹ያስተማረኝን ወገኔን በሙያዬ የማገልገል ሙያዊ ኃላፊነት አለብኝ›› በማለት ወደ አደጉበት ቀየ ተመልሰው ማገልገል ከጀመሩ ዓመታትን እንዳስቆጠሩ ነግረውናል። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የባለታሪካችን ማኅበራዊ ተቀባይነት እያደገ የመጣው። የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች እንደነገሩን ከሆነ የሰው ችግር ችግራቸው ነው፤ ከመቀበል መስጠትን፤ እንዲደረግላቸው ሳይሆን ለሰዎች በጎ ማድረግን ይመርጣሉ።

ዶክተር አያና በሚያስተዳድሩት የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ገንዘብ ሳይኖራቸው ሕክምና የተደረገላቻው ብዙ ናቸው። ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ…›› እንዲሉ በመስተንግዷቸው ተስፋ ሰንቀው የሚመለሱም በርከት ያሉ እንደሆኑ ይነገራል። የቀዝቃዛው ወላፈን የእንጅባራ ከተማ እድገት እንዲጎመራ እያሳዩት ያለው በጎ ሥራ ሌላኛው ተወዳሽ ተግባር ነው። ከከተማዋ እምብርት እስከ መናኸሪያው መታጠፊያ ድረስ ያለውን የአስፓልት መንገድ አካፋይ በአረንጓዴ ተክሎች አስውበዋል፤ ለዚህም ከ82 ሺህ ብር በላይ አውጥተውበታል።
ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ከተወጡ በኋላም በዘላቂነት እንዲንከባከበው ለከተማ አስተዳድሩ አስረክበዋል። ከተማዋን ሰንጥቆ ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር ከተማ የሚወስደውን አውራ መንገድ ተከትሎ ከተማዋ ጫፍ ላይ የሚገኘው የእንጅባራ ሆስፒታል መንገድ ለነብሰ ጡር እናቶችና ለሕሙማን ምቹ እንዲሆንም አስደልድለውታል። መንገዱ ተደልድሎ እየሰጠ ካለው ጥቅም በተጨማሪም አካፋ ይዘው እራሳቸው ቁመው ሲደለድሉ ያዩ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ ሊጠቀሙበት የሚችሉትን መንገድ የመጠበቅ የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስተማሩት ግንዛቤ እንደሚበልጥ ነዋሪዎች ነግረውናል።

ከዋናው አስፓልት መንገድ በስተግራ በኩል ወደ ሆስፒታሉ የሚያስገባው መንገድ አስቸጋሪና ኮረኮንች የበዛበት የነበር ቢሆንም ችግሩን የተረዱት ዶክተር አያና ጠጠር አስደፍተው መሬቱን አስቆፍረው ምቹ እንዳደረጉት ነው የከተማው ነዋሪዎች የሚናገሩት። መንገዱ ምቹ በመሆኑም ነዋሪዎቹን ከእንግልት ታድጓል፡፡ የአካባቢው ሰዎች ዶክተር አያና በራሳቸው ወጭ የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች መኖራቸውንም ነው የነገሩን።
12 የገንዘብ አቅም የሌላቸውን የአካባቢውን ተማሪዎች በየወሩ ከ200 እስከ 600 ብር ለትምህርት ወጭ ይከፍላሉ፤ ለተማሪዎቹ የኑሮ መደጎሚያም ይሰጣሉ፤ ለእነዚህ ተማሪዎች በአጠቃላይ በወር እስከ 43 ሺህ ብር ያወጣሉ። ከሚረዷቸው ተማሪዎች መካከልም ዓይነ ሥውራን ይገኙበታል። ከእነዚህ መካከል አራቱ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቀላቅለዋል። በምትካቸው ሌሎች ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠውልናል።
ማኅበራዊ ኃላፊነትን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው ሰዎችም ‹‹ልክ እንደ ዶክተር አያና ደግነትን ከሌሎች ሰዎች ሳይጠብቁ የመልካምነት ሐዋርያ ሆኖ መገኘት ለሆነለት መታደል ነው፤ ከበሬታን ያጎናጽፋል›› ብለውናል። እርሳቸው እየተወጡት ባለው ማኅበራዊ ኃላፊነት ወጥተው ሲገቡ በርካታ ሰዎች ምሥጋና ሲቸሯቸው መመልከታቸውንም ገልፀውልናል።

ዶክተር አያና ግን ‹‹የሠራሁት በዝቶ ሳይሆን ሕዝቡ ትንሽ ሞክረህ ስታሳየው አመሥጋኝ ስለሆነ ነው፤ ለዚህም ነው የሚቸረኝ ምሥጋና የበዛው›› ብለዋል። በማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ‹‹ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሁሉም ሰው ተግባር ሊሆን ይገባል›› የሚል ጠንካራ አቋምም አላቸው። ‹‹እኔ ደልቶኝ ሳይሆን ካለችኝ ትንሽ ነገር ለሌላቸው ማካፈል ስለሚያስደስተኝ ነው። ምንም ያክል ሀብት ቢሰበሰብ የምንኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ዑደት የተስተካከለ ካልሆነ እኛም ተጎጅ የምንሆንበት እድል ከፍተኛ ነው›› በማለት ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ለራስ መሆኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here