‹‹መንገዱ ከዲዛይኑ ውጭ እንዲሠራ ተደርጎብናል›› ሲሉ የቅራቅር ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡

0
59

የመንገዱ ዲዛይ የከተማውን የቀጣይ ዕድገት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ደግሞ መሪ ማዘጋጃ ቤቱ አስታውቋል፡፡

የፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ኢንጅነር መልካ መና የቀረበው ጥያቄ የመንገድ ስፋት ለውጥ እንጅ የቦታና የዲዛይን ለውጥ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከዳባት-አጅሬ -ቅራቅር-ከተማ ንጉሥ የሚሠራው መንገድ የቅራቅር ከተማን ማዕከል አድርጎ መጀመሪያ ዲዛይኑ ቢወጣም ከከተማው ውጭ እንዲያልፍ በመደረጉን በመግለጽ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

ለአብመድ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነዋሪዎች የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመጀመሪያው ዲዛይን ከተሞችን ማዕከል በማድረግ እንዲያልፍ በሰነድ እንዳስቀመጠ አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጅ መንገዱ በ2011 ዓ.ም ከከተማው በ2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ከተማ ንጉሥ እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡ ከዲዛይኑ ውጭ ከተማዋን ባገለለ ሁኔታ መንገዱ እንዲሠራ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑንም ነዋሪዎች ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ መንገዱ በዲዛይኑ መሠረት እና ማኅበረሰብን ተጠቃሚ በሚያደርግ አግባብ እንዲሠራ በተወካዮቻቸው አማካይነት ጥያቄ ቢያቀርቡም “ፕሮጀክቱ የሚሠራው መንግሥት ባመነበት እንጅ በሕዝብ ውሳኔ ሊሆን አይችልም” የሚል ምላሽ በወረዳው የሥራ ኃላፊዎች እንደተሰጣቸው ነው የገለጹት፡፡

‹‹በጊዜው ጥናቱ ሲካሄድም በከተማው መካከል ላይ የሚገኘውን መናኸሪያ እንደመነሻ ነጥብ እንዳደረገ በጨረታ ከቀረበው ሰነድ ላይ ተመላክቷል›› ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡ መንገዱ መጀመሪያ ከተጠናው በ2 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ እንዲሠራ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ጥያቄውንም ከ2011 ዓ.ም ጀምረው አቅርበው ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ነው ነዋሪዎች የተናገሩት፡፡

የቅራቅር ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን አራጋው እንደተናገሩት ደግሞ የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን በከተማዋ በሦስት አማራጮች ጥናት አድርጓል፡፡ ‹‹የከተማውን የቀጣይ ዕድገት ታሳቢ የሚያደርግ አማራጭ መንገድ እንዲሠራ ስምምነት ላይ ተደርሷል፤ ለዚህም ተጨማሪ 8 ሚሊዮን ብር ተጠይቋል›› ብለዋል፡፡
‹‹ጥያቄ አቅራቢዎች እንዲሠራ የሚፈልጉት መንገድም ዳገት የበዛበት እና አስቸጋሪ በመሆኑ እና በከተማዋ ዕድገት ላይም ተጽእኖ የሚያሳድር ስለሆነ በሌላ አቅጣጫና ወደፊት ከተማው በሚለማበት በኩል መንገዱ እንዲገባ ተደርገጓል›› ብለዋል አቶ ካሳሁን፡፡

ከአጅሬ-ቅራቅር-ከተማ ንጉሥ መንገድ ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሐንዲስ ኢንጅነር መልካ መና እንዳስታወቁት ደግሞ የቀረበው ጥያቄ የመንገድ ስፋት ለውጥ እንጅ የዲዛይን አይደለም፡፡ ‹‹በዲዛይኑ መሠረት የቅራቅር ከተማ የመንገድ ስፋት 18 ሜትር ነው፤ መሪ ማዘጋጃ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ ደግሞ በከተማው መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) መሠረት በ30 ሜትር ስፋት እንዲሠራለት ነው›› ያሉት መሐንዲሱ የመንገድ ዲዛይን ለውጥ አለመጠየቁን አመልክተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ጥያቄያቸው የውለታ ለውጥ በተቋራጩ ላይ እንደሚያመጣ ተረድተው ለውል ሰጭ (አሠሪው አካል) ማቅረብ እንደሚችሉም አስገንዝበዋል፡፡ ምንም ዓይነት የመንገድ ዲዛይን ለውጥ ሳይደረግ የተነሳው ቅሬታም ትክክል አለመሆኑን ነው ኢንጅነር መልካ የገለጹት፡፡ “መንገዱ ዲዛይንም ሲወጣለት ወደ መናኸሪያው ለማገናኘት ዳገታማ በመሆኑ እና ወደፊት የከተማዋን ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከከተማ አስተዳድሩ ጋር ስምምነት ላይ በመደረሱ ወደ ተግባር ተገብቷል” ብለዋል፡፡

ከዳባት-አጅሬ- ቅራቅር – ከተማ ንጉሥ 100 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን መስከረም 11/2011ዓ.ም ሥራ ጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱ ከዳባት-አጅሬ 43 ኪሎ ሜትር እና ከአጅሬ-ቅራቅር -ከተማ ንጉሥ 57 ኪሎ ሜትር በሁለት ተቋራጮች እየተሠራ የሚገኝ ነው፡፡ በሦስት ዓመት እንደሚጠናቀቅም በውለታው ተመላክቷል፡፡ የመንገድ ደረጃውም “ደብል ሰርፌስ ትሪትመንት” በተለምዶ “ሽሮ ፈሰስ” የሚባለው ደረጃ እንደሆነ ኢንጅነር መልካ አስታውቀዋል፡፡

ከአጅሬ-ቅራቅር -ከተማንጉሥ የሚሠራው 57 ኪሎ ሜትር መንገድ 1 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

ፎቶ:- ከፋይል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here