“ቃል የተገባልን የሥራ ቅጥርም አልተፈፀመልንም፡፡”  በክልሉ በሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በስኳር እና ኢታኖል ማምረት የሰለጠኑ ወጣቶች

0
96

‹‹ውለታ አልተገባም፤ እንደ ፕሮጀክትም የምናውቀው ነገር የለም፤ እያስተማሩ ያሉትንም አቁሙ የሚል መልዕክት ተላልፏል፡፡››  የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት

ማስረሻ እንደሻው በዳንግላ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በ‹ሱገር ክሮፕ ፕሮዳክሽን› ለአራት ዓመት ስልጠና እንደወሰደ ነግሮናል፡፡ በ2005 ዓ.ም በፌዴራል ደረጃ ‹‹ጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ትቀጠራላችሁ›› በሚል ውል መያዙንም ይናገራል፡፡ በወቅቱም ‹‹የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ገንዘቡን በልቶታል እና ሥራው (ፕሮጀክቱ) ውድቀት አጋጥሞታል›› በሚል የሥራ ቅጥር እንዳልተፈጸመ ቅሬታ አቅራቢው ተናግሯል፡፡

ፋብሪካው ወደ ሥራ እስከሚገባ ድረስ በሚል በደረጃ ሦስትና አራት የማሻሻያ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉንም ማስረሻ ጠቁሟል፡፡ የማሻሻያ ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላም የብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ወደ ኦሮሚያ ክልል በመሄድ በአርጆ ደዴሳ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ምዘናውን እንዲወስዱ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ደብዳቤ ጽፎ ልኳቸዋል፤ ተመዝነዋል፡፡

እንደ ማስረሻ ሁሉ በተመሳሳይ የትምህርት መስክ በደረጃ ሁለት ከቡሬ፣ ዳንግላ፣ እንጅባራና ዱርቤቴ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ስልጠናውን የወሰዱት 1 ሺህ 200 የሚደርሱ ወጣቶች ቅሬታውን እንዳቀረቡ ማወቅ ችለናል፡፡

የአማራ ክልል ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሻምበል ከበደ ‹‹የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ተማሪዎቹ የተግባር ተሞክሮ ስልጠናም ሆነ የትብብር ስልጠና ለመስጠት እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ፕሮጀክቱ ባለመጠናቀቁ ዝግጁ አይደለም፤ የምዘና ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ሲጠየቅም ፍቃደኛ አይደለም›› ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ ሲቀረጽ ስልጠና የሚሰጥባቸውን የሙያ ዓይነቶች እና የሙያ ደረጃዎች የሚያዘጋጀው ስኳር ኮርፖሬሽኑ ሆኖ የሙያ ደረጃ መሠረት ተደርጎ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ይሰጣል፤ ውጤታማነቱን በምዘና አረጋግጦ የሚቀበለው ኢንዱስትሪው ነው፤ መዛኝም እንዲመድብ የሚጠበቀው በኢንዱስትሪው ነው፤ በተደጋጋሚም በቃል እና በደብዳቤ ተጠይቋል፤ በክልሉ የሚመራ ተቋም ባለመሆኑም ተፅዕኖ መፍጠር አልተቻለም ብለዋል፡፡

የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አንተነህ አሰጌ ‹‹በዕውቀት ችግር ምክንያት ዜጎች ለችግር የተጋለጡበት ሁኔታ አለ፤ ይህን ፕሮጀክት እነማን ሲመሩት እንደነበር የታወቀ ነው፤ ወጣቶቹ በሸንኮራ አገዳ “አግሮኖሚ”፣ “ኢታኖል”ና በሌሎች ትምህርት መስኮች ሰልጥነዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የሰለጠኑ ተማሪዎችን በአንድ ፋብሪካ ለመቅጠር ያዳግታል›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ ‹‹ውለታ አልተገባም፤ እንደ ፕሮጀክትም የምናውቀው ነገር የለም፤ እያስተማሩ ያሉትንም አቁሙ የሚል መልዕክት ተላልፏል›› ብለዋል፡፡ ብዙ የሥራ ዕድል በሚፈጥር መስክ እንዲያሰለጥኑ ማሳወቃቸውንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ወደፊት ሌሎች ማስፋፊያ ሥራዎች (ፕሮጀክት) ሲጀመር ቅጥር ሊፈጸም ይችላል ካልሆነ በቀር አሁን ባለው ሁኔታ እንደማይቀጥሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹በጊዜው የነበሩ ኃላፊዎች በሌለ ገንዘብ የሥራ ዕድል እንሰጣለን የሚል ተስፋ ሰጥተው ነበር፤ ይህም አሁን የተፈጠረውን ችግር ወልዷል›› ብለው እርሻውም ሆነ ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገቡ ግን ተወዳድረው የሚቀጠሩበት ዕድል እንደሚኖር አመላክተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዋዩ ሮባ ‹‹አልተቀጠርንም የሚለው ቅሬታ በሀገሪቱ የሚከናወኑ ሌሎች የስኳር ልማት ሥራዎች ላይ ያጋጠሙ ችግሮች አካል ነው›› ብለዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም መሥራት ሲጀምሩ የሚያስፈልጉት ባለሙያዎችን ቁጥር ታሳቢ ተደርጎ በነበሩ ወጣቶቹ እንዲሰለጥኑ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡ ፋብሪካዎቹ ባለመጠናቀቃቸውም የሰለጠኑት ወጣቶች ሊቀጠሩ አልቻሉም፡፡ እንደ መተሐራ ሥራ ላይ ያሉ ስኳር ፋብሪካዎች እንኳ በየዓመቱ የሚሰለጥኑ ተማሪዎችን ማስተናገድ አይችሉም፡፡ ሠራተኛም የሚቀጠርበት ቦታ ሳይኖር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙም ተገቢ እንዳልነበረ አመልክተዋል፡፡

ወደፊት ፋብሪካዎቹ የሚሠሩበት ቦታ ላይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታሰቡን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አዳዲስ ፋብሪካዎች ሲጠናቀቁ በሚፈልጉት የሰው ኃይል መጠን የሚቀጥሩ ይሆናል፤ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካን በፍጥነት በማጠናቀቅ የሚቻለውን ያህል የሰለጠኑ ወጣቶችን ማስገባት ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡ ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባም የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥበትን ሁኔታ በማደራጀት ምዘናው እንዲሰጥ ማድረግ በቀጣይ የሚሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ማኅበረሰቡ ጉልበቱን፣ መሬቱንና ጊዜውን ሰጥቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዳልሆነም አንስተዋል፡፡

የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በታቀደው ጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት እንደ ሀገር ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሷል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here