“በምርጫ ሂደት ሕዝብ የሚፈልገው አማራጭ ብሔር ሳይሆን አማራጭ ሐሳብ ነው›::” የሕግ መምህር

0
67

ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሕዝብን ሕይወት በሚያሻሽሉ አጀንዳዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው በጉዳዩ ላይ ሐሳብ የሰጡን የሕግ መምህር ተናግረዋል፡፡

ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳ ሚያዝያ ላይ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በጊዜያዊ መርሀ ግብሩ አሳውቋል፡፡ ለመሆኑ በመጭው ሀገራዊ ምርጫ ለመወዳደር የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በምን ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባቸዋል? ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አብመድ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል መምህርና የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር ሰሎሞን ጓዴ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የምርጫ ቅስቀሳ በዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓት ፓርቲዎች ከተወዳዳሪዎቻቸው አብላጫ ድምፅ ለማግኘት ሐሳባቸውን ለመራጩ ሕዝብ የሚያሰሙበት ሂደት ነው፡፡ የሚቀርበው የቅስቀሳ ሐሳብ የመራጩን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንድ እርምጃ ከፍ ሊያደርግ የሚችል፣ የተጠናና ዘላቂነት ያለው የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አመላካች መሆን እንዳለበት መምህሩ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሙያዊ ማብራሪያው በሀገራችን ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ሲመዘን ተፈፃሚነቱ አጠራጣሪ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ እንደ መምህሩ ዕይታ በመጭው ሀገራዊ ምርጫ ተሳታፊ ለመሆን የተመዘገቡ ፓርቲዎች አብዛኞቹ ብሔር ተኮር ናቸው፡፡

ፓርቲዎቹ የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ሊያሻሽሉ ከሚችሉ፣ ሀገራዊ አንድነትንና ሉዓላዊነትን ከሚያስጠብቁ የፖሊሲ አማራጮች ይልቅ የወከሉትን ብሔር አነሳሽ ጉዳዮች ላይ ማተኮርን ለምርጫ ቅስቀሳ ይጠቀሙበታል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ነው መምህሩ የተናገሩት፡፡ “በምርጫ ሂደት ሕዝብ የሚፈልገው አማራጭ ብሔር ሳይሆን አማራጭ ሐሳብ ነው” ያሉትም ለዚህ ነው፡፡

ከዚህ በፊት የነበሩ አስተዳደራዊ ብልሽቶች፣ የተዛቡ የታሪክ ትርክቶች፣ ልዩነት ላይ ያተኮሩ የብሔር አደረጃጀቶች በየቀኑ አዳዲስ የግጭት መንስኤ እየሆኑ እንደሚገኙ የተናገሩት መምህር ሰሎሞን የአብዛኞቹ ችግሮች ምክንያቶች ጥቂት የሥልጣን ጥማት ያላቸው የፖለቲካ ልሂቃን እንደሆኑም ያምናሉ፡፡ የሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክም ይህን እንደሚያሳይ ነው ያስታወሱት፡፡

 

እናም የፖለቲካ ምሁራን ፍላጎት ሕዝብ ማገልገል ከሆነ በሀገር መቀጠል የሚያምኑና ሀገሪቱን ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሸጋጋር የመፍትሔው አካል መሆን እንዳለባቸው ነው የመከሩት፡፡ ለዚህ ደግሞ በዕውቀት ላይ የቆመ፣ በሐሳብ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር መፍጠር፣ ለከተሜውም ሆነ ለአርሶ አደሩ፣ ለተማረውም ሆነ ላልተማረው የሚሆን ጠንካራ ፖሊሲ ሐሳብ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት ጫፍ ደርሶባቸዋል በሚባሉት ሀገራት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፓርቲዎች የሚያነሷቸው ዐበይት ነጥቦች ጠንካራ ማኅበራዊ አንድነት በሕዝብ መካከል እንዲኖር ማድረግ፣ ሀገርን መገንባት፣ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል … መሆኑንም ነው መምህር ሰሎሞን ያስገነዘቡት፡፡

እየታየ ያለውን የብጥብጥ አዝማሚያ ለመቅረፍም ሁሉም ፓርቲዎች በከፋፋይ ሐሳቦች ላይ እንዳያተኩሩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here