በሰሜን አሜሪካ የተቋቋሙ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አደረጃጀቶችን ለመደገፍ ኤምባሲው ዝግጁ መሆኑን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ተናገሩ፡፡

0
25

በሰሜን አሜሪካ የተቋቋሙ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አደረጃጀቶችን ለመደገፍ ኤምባሲው ዝግጁ መሆኑን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ተናገሩ፡፡

በአማራ ክልል የዳስ ትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር የሚያችል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሀ ግብሩ የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እየታደሙ ይገኛሉ፡፡ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ለታዳሚያኑ ባስተላለፉት መልዕክትም ሁሉም ለሕዝብ ሕይዎት መሻሻል የሚያስችሉ በጎ ተግባራትን በተደራጀ መልኩ እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የተቋቋሙ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አደረጃጀቶችን ለመደገፍም ኤምባሲው ዝግጁ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው በበኩላቸው ከዚህ በፊት ባለመደራጀት በአማራው ላይ ይደርሱ ከነበሩ ችግሮች በማመር ሁሉም በየዘርፉ ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠርና የሕዝቡን ኅልውና ማስጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች በተካሄዱ ውይይቶች በውጭ ሀገር የሚኖሩ ወገኖች ለሕዝቡ ኑሮ መሻሻል እና ለክልላቸው ልማት ያላቸውን ቁጭት መመልከታቸውን የተናገሩት አቶ ዮሐንስ መነሳሳቱን ወደ ውጤት መቀየር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በሰሜን አሜሪካ በተካሄዱት ዝግጅቶች ሁሉ ለክልሉ ልማት እና ዕድገት እንዲሁም ለአማራ ሕዝብ አንድነት በመቆርቆር በኃላፊነት ሥሜት ሲሰሩ ለነበሩ ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ የአማራ ማኅበራት፣ መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎችም ተሳትፎ ያደረጉ ግለሰቦች እና ማኅበራትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የአልማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፈንታ ደግሞ በልማት መኅበሩ የታቀዱ ተግባራት እውን እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡ በሰሜን አሜሪካ የአልማ አደረጃጀትም ድጋፉን እና የልማት ተሳትፎውን በማቀናጀት ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያስችል፣ ለዚህም ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አዲስ የተመረጡ የአልማ አደረጃጀት መሪዎች ሥኬታማ ሥራ እንዲያከናውኑ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች እገዛ እንዲያደርጉላቸውም ነው አቶ መላኩ የጠየቁት፡፡

በአማራ ክልል የዳስ ትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር ታስቦ በዋሽንተን ዲሲ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ታዋቂ አርቲስቶች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን እያቀረቡ ነው፤ ምሁራን፣ ባለሃብቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም እየታደሙ ይገኛሉ፡፡

ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ-ከዋሽንግተን ዲሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here