በሰው ሰራሹ ሞሉ ሐይቅ ላይ ወጣቶች በዓሣ ማስገር እንዲሰማሩ እየተሠራ መሆኑን የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳድር አስታወቀ፡፡

0
22

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 30/2012ዓ.ም (አብመድ) የሞሉ ሐይቅ በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ ነው የሚገኘው፡፡ ከአጣዬ ከተማ በአራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፤ ሐይቁ የተፈጠረበት ቦታ ረግረጋማ መሬት በመሆኑ ለግጦሽ ዳርዳሩን ደግሞ አርሶ አደሮች ሸንኮራ በማልማትና የተለያዩ አዝዕርቶችን በመትከል ይጠቀሙበትም ነበር፡፡

በ1978 ዓ.ም በኩባ ሙያተኞች በመታገዝ ለመስኖ አገልግሎት ግድብ መገንባቱን ተከትሎ ቦታው ቀስ በቀስ ወደ ሐይቅነት ተቀየረ፤ በአቅራቢያ ባለው የሞሉ ተራራ ሥም ሐይቁ መሠየሙን በኤፍራታና ግድም ወራዳ የባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የሆቴል ብቃት ማረጋገጥ ባለሙያው ታለጌታ ለጤ ወልደማርያም ተናረዋል፡፡

ሞሉ ሐይቅ 69 ነጥብ 35 ሄክታር መሬት ስፋት አለው፤ ጥልቀቱ አራት ሜትር ነው፤ ወደ ማዕከሉ ሲገባ ግን እስከ ስድስት ሜትር ድረስ ጥልቀት አለው፤ የውኃ መጠኑ ደግሞ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው፤ የቀረሶ ዓሣ ደቡብ ወሎ ሐይቅ እንዲመጣ ተደርጎ በሐይቁ እየረባም ነው፤ ሐይቁ በአጣዬ ከተማ መንገድ ዳር ያለና የወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር መስመርን የሚነካ በመሆኑ ለጉብኝትም ምቹ ነው፡፡

ቦታውን የሚያስተዋውቅ ዘጋቢ ፊልም መሠራቱን ለሚመጡ እንግዶች ለማስተዋወቅ መሞከሩን ከወረዳው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፤ የሐይቁን ምስል (ፎቶ) አዘጋጅቶ ለማሳወቅ ጥረቱ የተደረገ ቢሆንም ሀገራዊ የሆነና ሰፋ ያለ የማስተዋወቅ ሥራ ግን አለመሠራቱን አቶ ታለጌታ ገልጸዋል፡፡ ወደፊትም በትንሹ በማልማት ተጠቃሚ የሚኮንበት ዕድል ስላለ ከወረዳው ኃላፊዎች ጋር እየመከሩ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

ከዚህ በፊት በኤፍራታና ግድም ወረዳ ሞሉ ሐይቅ በሚገኝበት አቅራቢያ የበርግቢ ቀበሌ ወጣቶች ዓሣ እርባታ ልማት ሥራ ይከውኑበት እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ሥራው የተቋረጠው በፍላጎት ማጣት መሆኑን የኤፍራታና ግድም ወረዳ ቴክኒክና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን አልታዬ ገልጸዋል፡፡

ስምንት ሺህ ጫጩት ዓሣ ከሐይቅ በማምጣት ወደ ሞሉ ሐይቅ ገብቶ እና በወረዳው እንስሳት ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤትና በግብርና እድገት መርሀ ግብሩ (ኤጂፒ) መሠረት የጀልባ ድጋፍም አግኝተው ነበር፡፡ ሌሎች ወጣቶችንም በሐይቁ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ለማደረጀት ተሞክሯል፤ ፍልጎቱ ግን ወዲያው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥራ ላይ በመሆኑ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል፡፡

አጣዬ ከተማ ዓሣ መሸጫ ሱቅ ተዘጋጅቶም ነበር፤ በግብርና ጽሕፈት ቤት ባለሙያ በመታገዝ የገበያ ችግር እንደማያጋጥም መታወቁም ተነግሯል፡፡ ሆኖም ወጣቶቹ ሥራውን መቀጠል እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል፡፡ የተዘዋዋሪ ፈንዱን በመጠቀም ወጣቶች እንዲሠሩ ጥረት እየተደረገም ነው፡፡
ከአጣዬ ከተማ አስተዳድር አርአያ የሚሆኑ ወጣቶችን ከኤፍራታና ግድም ወረዳ ከገጠሩ አካባቢ የመጡ ወጣቶች ጋር በማቀላቀል በዓሣ እርባታ እንዲሰማሩ መታሰቡንም ነው የተናሩት፡፡ ጥቂት ወጣቶች ፍላጎታቸውን ማሳየታቸውን የተናገሩት አቶ ሰሎሞን አዋጪነቱን በባለሙያ በማስረዳት ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው፡፡ የወጣቶቹ አቋም መልካም ምላሽ ካገኘም አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራው ለማሠማራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here