በቃል ሳይሆን በሥራቸው ብዙዎቹን ማሳመን እና ከጎናቸው ማሰለፍ የቻሉትን የሀገር ባለውለታ መቼ እናመሠግናቸው ይሆን?

0
113

ሰቆጣ ስያሜዋን አገኘች ተብለው ከሚነገሩ መላምቶች አንዱ ‹‹ሳ ቊጠ›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ፋጥዝጊ ከሚባል ከፍታ ቦታ ሆኖ ቁልቁል ስትታይ ‹ከታች ያለች እርጥበታማ ቦታ› የሚል ትርጎሜን ያስገኛል፡፡ ይህ ደግሞ ሰቆጣን ለሁለት ከሚከፍላት ወንዝ የሚመነጭ ነው፡፡ በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ለተመሠረተችው ከተማ ይህ ወንዝ ለከተማዋ መመሥረት የራሱ ሚና አለው፡፡ ወንዙ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ እስከ ባለፉት ጊዜያት የከተሜነት መስፋፋት ማዶ ለማዶ የተመሠረቱ መንደሮች ቆሻሻ መድፍያ ሁኖ አገልግሏል፡፡ ለንፁህ መጠጥ ውኃ መገልገያ እና ለንፅህና መጠበቂያ ሲያገለግል የነበረው ወንዙ የቆሻሻ መጣያ፣ ሽሽግ የመጸዳጃ ቦታ መሆን ሲጀምር ለጤና ጠንቅ የሆነ ሽታ የሚፈጠር አስቸጋሪ ቦታ መሆን ጀመረ፡፡ ለከተማዋ ውበትም እንቅፋት ሆነ፡፡  ለ20 ዓመታት በመንግሥት ሥራ አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር እና ሰቆጣ ሲሠሩ የነበሩት አቶ አዲሴ ሁሴን ስፍራውን ሲመለከቱ እንደመንገደኞች ሁሉ ዝም ብለው ማለፍ አልወደዱም፡፡

በጎርፍ የተቦረቦረውን የከተማዋን አማካይ ወንዝ ድንጋዩን ከአፈሩ ጋር እያዋደዱ ለአምስት ዓመታት እርከን መሥራት ቀጠሉ፡፡ በክረምት ወቅት ችግኝ እየተከሉ እርከኑን አስተማማኝ አደረጉት፡፡ ዛፎቻቸውን አንድ ጊዜ ከቤታቸው ሌላ ጊዜ ከወንዙ እየቀዱ ውኃ ማጠጣት የሁልጊዜ የቤት ሥራቸው ሆነ፡፡

ወንዙን በግንብ አጥረው ችግችን፤ አበቦችንና አትክልትና ፍራፍሬ መደቦችን አዘጋጅተው ማልማታቸውን ቀጠሉ፡፡ የመንግሥት ሥራቸውንም ከወንዙ ባዩት ተስፋ ምክንያት አቋረጡት፡፡ አፍንጫቸውን ይዘው ይሻገሩ የነበሩ ነዋሪዎች ከጥቂት አፈርና ድንጋይን የማከም የቤት ሥራ በኋላ ንፁህ አየር ከመልካም መዓዛ ጋር መተንፈሱ አስደስቷቸዋል፡፡ ‹‹ጋሽ አዲሴ በርታ›› እያሉ የሚሄዱት ሰዎች ዓላማቸውን ለማሳካት ኃይል እንደሆኗቸው ያስታውሳሉ፡፡

ይህን ጅምር ሁነት የከተማ አስተዳድሩ ፈቅዶ ወደ መናፈሻነት ሲቀየር በከተማዋ አዲስ የመናፈሻ ዘውግን ተቆናጥጧል፡፡ ንፁሁን አየር ያለበት ነፋሻ ቦታው ለተማሪዎች ለንባብና መዝናናት ለሚፈለጉ ደግሞ በከተማዋ ባልተለመደው መልኩ አረንጓዴ መናፈሻ የመጀመሪያ ምርጫቸው ሆኗል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቀለበት፣ የሠርግ፣ የልደት እና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ማድመቂያ ሁኗል፡፡ ይህ የአቶ አዲሴ ተግባር ለከተማዋ አረንጓዴ ልማት መነቃቃት አብነት ሁኗል፡፡ አቶ አዲሴን ተከትሎ በሰቆጣ ከተማ ወንዝ ላይ የሚሠሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በተለያዩ ሰዎች በመዘውተሩ የከተማዋን አየር ንብረት እንዲቀየር ዕድል ፈጥሯል፡፡

አቶ አዲሴ አካባቢውን ያለመሰልቸት ሌሊት እና ቀን አስውበው እና አሳምረው፤ የተጎዳን መሬትም እንዴት ማልማት እንደሚቻል ሠርተው በማሳየታቸው ‹ታታሪ ጀግና› በመባል የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል፡፡ ለራሳቸው ትልቅ የገቢ ምንጭ፤ ከ35 ሺህ ሕዝብ በላይ ለሚኖሩባት ሰቆጣ ከተማ ደግሞ ከከንፈር መምጠጫነትና ከአፍንጫ ማፈን ወጥቶ ንፁህ አየር መቀበያ፣ ለአዕምሮ መቀየሪያ ምቹ ቦታ ሁኗል፡፡

ትዝብታቸውን ያጋሩን ግለሰቡ ‹‹በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት በ410 እንደተቆረቆረች የሚነገርላት የሰቆጣ ከተማ ከአክሱም ጋር የተያያዘ ታሪክም እንዳላት ይነሳል፡፡ በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት (ከ495-525 ዓ.ም) ከአንድ አለት ተፈልፍሎ እንደተሠራ የሚነገርለት ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከ500 ዓመታት በላይ የሚቀድመው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን መገኛም ናት ሰቆጣ፡፡ ለዚህች ታሪካዊት ከተማ አንድ ውለታ ማድረግ እንዳለባቸው በማመን ነበር ወደ ወንዝ ልማት የገቡት፡፡

‹‹የሰቆጣን ከተማ ከበረሃማ አካባቢዎች ጋር አስተሳስሮ ለመናገር አይቻልም፤ የከርሰ ምድር ውኃው ብዙ እንድትለማ የሚያደርግ ነው›› ያሉት አቶ አዲሴ በእንደዚህ ዓይነት አካባቢዎች የአረንጓዴ ልማት መዝናኛዎች ለቱሪስቶች እና ለነዋሪዎች የደስታ ምንጭ እንዲሆኑ በማለም እየተጉ ነው፡፡

ሰፊውን ሸለቆ በዛፍ እና በአትክልቶች ውበት አድምቆ፣ የተቃጠለውን አየር አቀዝቅዞ ለአካቢው የደስታ በረከትን የረጨው የአቶ አዲሴ መናፈሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የነበሩትን ሁለት አስተያየቶች ዛሬም ያስታውሱታል፡፡

ልፋቱን ዓይተው በውስጣቸው ‹‹እንዲያው ምን ሊያገኝ ይሆን በቆሻሻ ቦታ ሲደክም የሚኖረው? አንዳች ነገርም ሳይመታው አይቀርም›› እያሉ በአንደበታቸው ደግሞ ‹‹በርታ!›› እያሉ የሚያጀግኑ ሰዎችን የሥራቸውን ውጤት በማሳየት ሐሳባቸውን እንዲቀይሩ አድርገዋል፤ በምፀት ሲሳለቁባቸው ለነበሩ ሁሉም ነገር እንደሚቻል በማሳየታቸው ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል፡፡

ስለአቶ አዲሴ የሚያውቁት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው አቶ ፍስሐ ሀብቱ ‹‹መቀመጥ መቆመጥ›› ነው የሚል  አመለካከት ያላቸውን የግለሰቡን አይደክሜነት እያስታወሱ ‹‹ይህ ቦታ እንዲህ አምሮ እና ደምቆ  ከመታየቱ በፊት በአካባቢው ለማለፍ አፍንጫን አፍኖ በፈጥነት ነበር፡፡ በዓይን ለማየት ዘግናኝ ነው የነበረው፤ይህ አካባቢ አዝኖ የደረሰለት የቁርጥ ቀን ልጅ  ስላገኘ ታክሞ ዳነ እንጂ ወላጆች ለልጆቻቸው ወደ አካባቢው እንዳይሄዱ ከሚመክሩባቸው ለደኅንነት እና ለጤንነት አስጊ እና አስታዋሽ ካጡ  ቦታዎች ውስጥ ነበር›› ብለዋል፡፡ አቶ ፍስሀ ‹‹እርሱ ግማሽ ዕድሜውን ከዚህ ቦታ ነው ያሳለፈው፡፡ በዚህ ሰዓት በዚህ የመዝናኛ ሎጂ ተገናኝተን ስናወራ ከዚህ በፊት በፌዝ ሳልፍ እንደነበር ስነግራቸው የብዙ ሰዎች ሐሳብ እንደሆነ ያጫውቱኛል›› ብለዋል፡፡

አቶ ፍስሐ ‹‹እኔ የተረዳሁት ‹ታላቅ ሰው ከባድ ችግርን ወደ ትንሽ፤ ትንሿን ችግር ደግሞ ወደ ምንም የመቀየር ኃይል ያለው ነው›፡ የሚለውን ነው›› በሚል ነበር ምስክርነታቸውን የነገሩን፡፡

አፉን ከፍቶ ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ በአርምሞ ‹‹አድኑኝ!›› ለማለት የዳዳ የሚመስል ቦታ ዛሬ ፈጣሪው መልእክተኛ ልኮለት አፉ እና አካሉ ሞልቶለት በሚማርኩ የጽጌረዳ አበባዎች ደምቆ እና አሸብርቆ ሲታይ  እውነትም ነዋሪዎች እንደሰየሙለት ‹‹የገነት ምሳሌ›› መባሉ አያንስም፡፡ በውስጡ እና በዙሪያው ባለውለታው የተከሏቸው የፍራፍሬ እና የጓሮ አትክልቶች ለዓይን እርካታ፤ ለአፍንጫ ማራኪ ሽታ ፈጥሮ የትናንቱን  ትቢያ እና መጥፎ ጠረን ለውጦ በመልካም  መዓዛ በመተካቱ ሁሌም ግለሰቡን ለማድነቅ እንደሚገደዱ የከተማዋ ነዋሪ አቶ አረጋዊ ጥዑማይ ተናግሯል፡፡

ወጣቱ አቶ አረጋዊ ቦታው ከዚህ በፊት እንስሳት እና ሕጻናት በጎርፍ አደጋ ሲወሰዱ የነበሩበት ቦታ መሆኑን እንደሚያውቅ እና አሁን ግን ሙሉ በሙሉ የበርካታ ዕፅዋት የአትክልትና ፍራፍሬዎች መገኛም መዝናኛም በመሆኑ መደነቁን ነው የገለጸው፡፡

በሰቆጣ ከተማ አስተዳድር የንጽህና እና ውበት ሥራ ሂደት ኃላፊ ጌታወይ ሞጎስ ደግሞ ‹‹ስለእውነት ነው የምነግርህ፤ አቶ አዲሴ እጅግ ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር አላቸው፤ መናፈሻው ከውስን ዓመታት በፊት እጅግ ለጤና አስጊ እና ለሰዎች ድኅንነት አስቸጋሪ የነበረ አካባቢ ነበር፤ ዛሬ ግን  ለብዙዎቻችን  በሚያስገርም ሁኔታ ይህ የምናየው መናፈሻ ‹ምድረ ገነት› እያልን የምንጠራው ሆኗል›› ብለዋል፡፡ ‹‹ምንም እገዛ ሳይደረግላቸው በግል አቅማቸው ብቻ ውብ አካባቢ መፍጠር ችለዋል፡፡›› ከአቶ አዲሴ ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎችም ተሞክሮ በመውሰድ የሠሩት የአረንጓዴ ልማት ሥራ ግለሰቡ ተከታዮችን ያፈሩ ጀግና እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ሥራየ የደስታየ ምንጭ ነው›› የሚሉት አቶ አዲሴ ደስታቸው ለሌሎች ሰዎችም ደስታን በመፍጠሩ ዓላማቸው መሳካቱንም ተናግረዋል፡፡ ቀጣይ ዘመናዊ ሎጂዎችን ለመገንባት ዕቅድ ያላቸው አቶ አዲሴ ‹‹ዛሬ ካሳካሁት ይልቅ ነገ ለማሳካው ነገር ጥረት ጀምሬያለሁ›› ብለዋል፡፡ በአንድ ግለሰብ ጥረት አስገራሚ ለውጥ ማምጣት ከተቻለ የብዙዎች ጉልበት ብንጠቀም ምን ያክል ውብ ሀገርን እና አካበቢን በፈጠርን ነበር፡፡

ዘጋቢ፡- ብርሃኑ ደባሽ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here