አኩሪ አተርን በመጠቀም በቀን 15 ሺህ ሊትር ዘይት የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው 600 ኩንታል መኖ እንደሚያቀርብም ነው የተገለጸው፡፡ በሁለት ፈረቃ ለ120 በቋሚ እና ለ60 ሰዎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ ለቋሚ ሠራተኞች በአማካይ እስከ 4 ሺህ ብር ለጊዜያዊዎቹ ደግሞ እስከ 2 ሺህ 400 ብር እንደሚከፍሉ የፋብሪካው ባለቤት አቶ ጌታሰው አያሌው ገልጸዋል፡፡

የፋብሪካው ሠራተኛ ወይዘሮ ኢትዮጵያ በለጠ ከዚህ በፊት ይሠሩበት በነበረው ድርጅት ዝቅተኛ ክፍያ ይከፈላቸው እንደነበር ገልጸው ከዚህ ፋብሪካ ከተቀጠሩ በኋላ ግን የተሻለ ደመወዝ እየተከፈላቸው መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡ በፋብሪካው ሠርተው የሚያሠሩ ሙያተኞች ስለሚገኙ ትምህርትና ልምድ በመቅሰም በኩልም ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆንላቸው ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በግብዓትነት አኩሪ አተር፣ ሰሊጥና ሱፍ እንደሚጠቀሙም ነው የገለጹት፡፡ በዚህ ጊዜ ግብዓቱን በቀጥታ ግዢ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ እየፈጸሙ ነው፡፡ ወደፊት ግን መጋዘን በመገንባታቸው ከቋራ፣ ጃዊ እና ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ለመግዛት ዝግጅት ማድረጋቸውን የፋብሪካው ባለቤት አቶ ጌታሰው ተናግረዋል፡፡ ገበያውን እያጠኑ ትንተና መሥራታቸውን የገለጹት አቶ ጌታሰው በተሻለ ዋጋ በቀጣዮቹ ሦስትና አራት ቀናት ውስጥ ለገበያ እንደሚያቀርቡ አመላክተዋል፡፡ በቀጣይ ቀናትም ዋጋውን ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የጌታሰው አያሌው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ፕረሸት ቲባሪ የዘይት አመራረት ሂደቱ ከኬሚካል ንክኪ ነፃ እንደሆነ በመግለፅ በተሻለ ጥራት ዘይቱ እንደሚመረት አስገንዝበዋል፡፡ ዘይቱ ዓለማቀፍ ደረጃን አሟልቶ እየተመረተ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡ ፋብሪካው ከኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የምስክር ወረቀት ተቀብሏል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥራት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚያገኝም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የሕዝብ ምግብ ዘይት ፍላጎቱ አራት በመቶውን ብቻ እያመረተች እንደሆነ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ይህ ፋብሪካ በተወሰነ መልኩ የዘይት ፍላጎቱን ማሟላት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡ ወደፊትም ፋብሪካውን በማስፋትና አቅሙን በማሳደግ ፍላጎቱን የማሟላት ሐሳብ እንዳለም ነው የገለጹት፡፡

የፋብሪካው ግንባታ በ2009 ዓ.ም ነው የተጀመረው፡፡ 410 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበታል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here