በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ አሜሪካ ያሳየችው አቋም ከተሰጣት ኃላፊነት በላይ መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ተናገሩ፡፡

0
21

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2012 ዓ.ም (አብመድ) አምባሳደር መለስ ዓለም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን፣ የድርድሩን ሁኔታ እና የአሜሪካን የአደራዳሪነት ሚና በተመለከተ ከምሥራቅ አፍሪካ ዘጋቢ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካው ጋዜጠኛ ግድቡ ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ ላነሳላቸው ጥያቄም ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ ያላት ተስፋ አሁን የምትገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ እንደሆ አስረድተዋል፡፡ ግድቡ ድህነትን ድል ለመንሳት ወሳኝ ስለመሆኑም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ እንደሆነ የተናገሩት አምባሳደር መለስ ኢትዮጵያ ከጠቅላላው ሕዝቧ ውስጥ ከ65 ሚሊዮን በላዩ መብራት ባለማግኘቱ ከዓለም በስተጀርባ ሆኖ እየኖረ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡ ታዲያ በጭስ እየተበከለ፣ በጤናውም በጉልበቱም እየተጎዳ ያለውን ሕዝብ ከድህነት አውጥቶ ኢኮኖሚው ጠንካራ እንዲሆን በዓባይ ወንዝ ላይ የሚሠራው ግድብ ወሳኝ እና የኅልውና ጉዳይ እንደሆነ ዓለም ሊረዳው እንደሚገባ ነው ለመገናና ብዙኃኑ ያስገዘነቡት፡፡ ግድቡ በየዓመቱ 32 በመቶ የሚያድገውን የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለመመለስ ተስፋ እንደተጣለበትም ነው አምባሳደር መለስ ዓለም ያብራሩት፡፡
ግድቡ ሥራ ለመፍጠር፣ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጤናማ ኑሮ እንዲኖር ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ በመግለጽም የግድቡ መጠናቀቅ የሀገር ግንባታና የኅልውና ጉዳይ ነው የሚባልበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ግድቡን ድንገት የገባችበት ሥራ እንዳልሆነ ዓለም ሊገነዘበው ይገባል፤ ከ1960 (እ.አ.አ) ጀምሮ ጥናቶች ተደርገዋል፤ የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ጨምሮ ባደረጉት ጥናት ግድቡ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ጉዳት እንደማያደርስ ነው ያረጋገጡት፤ ኢትዮጵያ በተናጠልም ከግብጽ ጋርም አጥንታለች፤ ጥቅሙ ትልቅ እንደሆነም ተረጋግጧል” ብለዋል አምባሳደሩ በቃለ ምልልሳቸው፡፡

በአሜሪካ ለቀረበው የመጨረሻ ድርድር ኢትዮጵያ ለምን እንዳልተገኘች ሲጠየቁም “አሜሪካውያን የድርድሩ አመቻቾች ናቸው፤ ኢትዮጵያ ያለችው በሀገር ውስጥ መምክር ስለሚገባ ጊዜ ይሰጠን ነው፤ ይሁን እንጅ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዋና ጸሐፊ ራሳቸውን እንደ ዋና ተዋናይ አድርገው መጡ፤ ይህ ትክክል እንዳልሆነ ተገልጧል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ግልጽ አቋሟን ማስቀመጧን፣ የድርድር ሰነዱ መዘጋጀት ያለበትም በሦስቱ ሀገራት በኩል ብቻ መሆን እንዳለበት መግለጧን ነው አምባሳደሩ የተናገሩት፡፡ በተለይም የአሜሪካ ሚና ከታዛቢነት ወጥቶ ወደ ዋና ተዋናይነት መቀየሩ ግልጽ ሲሆን ኢትዮጵያ ይህን እንደማትቀበለው ማስታወቋንም ግልጽ አድርገዋል፡፡ የሀገራቱ ድርድር እንዳላበቃና ማስገደድ የሚባለውም ተቀባይነት እንደሌለው አስገንዝበዋል፡፡ “ድርድሩ የኢትዮጵያን ጥቅም እስካላስከበረ ድረስም ተገድዳ አትቀበለም፤ ጉዳዩ ሀገርን እና ሕዝብን ዝቅ አድርጎ ማየት ነው፤ የሀገሪቱንም ሉዓላዊነት ተዳፍሯል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትፈልገው ድርድሩ በእውነት ላይ ተመሥርቶ ሁሉንም ተጠቃሚ በሚደርግ መልኩ እንዲካሄድ እንደሆነም አስገነዝበዋል፡፡
ስለሆነም በመጀመሪያው የሕዳሴው ግድብ የውኃ አሞላል ላይ ተቀራርቦ እና ተማምኖ መደራደር እንደሚያስፈልግ፣ የቅኝ ገዥዎች ሕግ ይፈጸም የሚለው የግብጽ አካሄድ ግን በተፋሰሱ ሀገራት ተቀባይነት አንደሌለው ነው አምባሳደር መለስ ዓለም የተናገሩት፡፡

ግብጽ በየዓመቱ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውኃ መጠን ማግኘት ትፈልጋለች ሉት አምባሳደሩ ይህም የዓባይ ወንዝን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎት በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ዩጋንዳን እና ሌሎችም የተፋሰሱ ሀገራት እንደማይቀበሉትም አስታውቀዋል፡፡ መተባበር ብቸኛው መውጫ መንገድ በመሆኑ ተባብሮ መሥራት ላይ ሀገራት ቢያተኩሩ እንደሚሻልም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

በምሥጋናው ብርሃኔ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here