በአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 239 የላቦራቶሪ ምርመራ አንድ ሰው የኮሮናቫይረስ ተገኝቶበታል።
ቫይረሱ የተገኘበት የ28 ዓመት ወጣት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ክትትል ሲደረግለት የነበረ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል።
ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በክልሉ ለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከላት የሚገኙት ሁሉም ሰዎች በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን፣ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የገባ ታማሚም አለመኖሩን ቢሮው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል።
በአማራ ክልል እስከ ዛሬ ግንቦት 30/2012 ዓ.ም ድረስ ለ3 ሺህ 31 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎ በ119 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ታውቋል። ከእነዚህ መካከል 23 ሰዎች አገግመዋል፤ እስካሁን በክልሉ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ ሰው አለመኖሩንም የጤና ቢሮው መረጃ ያመላክታል።
እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ከምዕራብ ጎንደር ዞን (97) (ይህ አካባቢ ከሱዳን የሚገቡ ኢትዮጵያውያን በለይቶ ማቆያ የሚቆዩበት ነው)፣ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን (አንድ)፣ ከጎንደር ከተማ (ሦስት)፣ ከደሴ (ሁለት)፣ ከባሕር ዳር (አራት)፣ ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር (ሦስት)፣ ከሰሜን ሸዋ ዞን (ሁለት)፣ ከሰሜን ወሎ ዞን (አራት)፣ ከደቡብ ጎንደር ዞን (አንድ)፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር (አንድ) እና ከምሥራቅ ጎጃም ዞን (አንድ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪ) መሆኑ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ደግሞ እስከዛሬ ለ142 ሺህ 960 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፤ በአጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥርም 2 ሺህ 20 ደርሷል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 647 በሕክምና ላይ ይገኛሉ፤ 27 ሕይወታቸው አልፏል፤ 344 ደግሞ አገግመዋል፡፡ 32 ሰዎች በጽኑ ሕክምና ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡