በክልሉ የማሌዥያን የኢንቨስትመንት መስፋፋትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ተሞክሮ ለመተግበር 51 ፕሮጀክቶች ተለዩ፡፡

0
37

የማሌዥያን የኢንቨስትመንት መስፋፋትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ተሞክሮ ለመተግበር የሚያስችል የቤተ ሙከራ ወይይት ባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡

ተሞክሮውን ለመተግበር ባለፉት ስድስት ወራት በአማራ ክልል መንግሥት እና ‹‹ቢግ ዊን›› በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጥናት ሲደረግ ቆይቶ ለትግበራ 51 ፕሮጀክቶች መለየታቸው ተገልጧል፡፡ የቤተ ሙከራ ውይይቱ ከባለሀብቶች እና ከሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ነው የተደረገው፡፡

የጥናቱ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሞገስ ተኬ እንደገለጹት ጥናቱ ከ2010 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ከማሌዥያ እና ከክልሉ ከተለያዩ ቢሮዎች በተመረጡ ባለሙያዎች ተካሂዷል፡፡ አቶ ሞገስ እንደገለጹት ተሞክሮው የተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እና ባለሀብቶች በአንድ ማዕከል ተገናኝተው በችግሮቻቸው ላይ የሚመክሩበት እና የአሠራር ማዕቀፍ የሚዘረጉበት ሂደት በመሆኑ የክልሉን ኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘላቂነት ያረጋግጣል፡፡

ተሞክሮውን ለመተግበር ከተለዩት 196 ባለሀብቶች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መስፈርቶችን ያሟሉ የተባሉ 51 ፕሮጀክቶች መለየታቸውን ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡ አቶ ሞገስ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2018 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት  34 ቢሊዮን ብር ማፍራት ያስችላቸዋል፤ ለ146 ሺህ 386  ዜጎች ደግሞ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡   ፕሮጀክቶቹ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በኃይል አቅርቦት መስኮች እንዲሰማሩ በጥናቱ ተለይቷል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ በሰብል፣ በእንስሳት፣ በወተት ሀብት ልማት እና በግብርና ምርት ማቀነባር ዘርፎች ላይ በክልሉ ተግባራዊ ያደረጋል፡፡ ሥራውንም ለማዘመን የመሬት አቅርቦት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሲሠራ መቆየቱን አቶ ሞገስ ጠቁመዋል፡፡  በቀጣይ የትግበራ ምዕራፎች ደግሞ ሌሎች ዘርፎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ አስተባባሪው ነግረውናል፡፡

ሥራውን ተግባራዊ ለማድርግ ለርእሰ መሥተዳድሩ ተጠሪ የሆነ የክትትል ቡድን እንደሚቋቋም ተገልጧል፡፡ ቡድኑም አፈፃጸሙን በየጊዜው ሪፖርት ያቀርባል፡፡  ውጤታማ ባልሆኑ ተቋማት ላይም እርምጃ ይወስዳል፡፡ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከአበዳሪ ተቋማት፣ ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት እና ከተለያዩ  ሴክተሮች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል፡፡ ፕሮጀክቶችም ከሁለት ሳምንታት በኋላ ወደ ተግባር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ማሌዥያውያን ከ2009 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ባሉት 7 ዓመታት በሠሩት ሥራ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት መካከል መሰለፍ እንደቻሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here