በዋሽንግተን ዲሲ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አደረጃጀት ተቋቋመ፡፡

0
15

በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የአልማ አደረጃጀት ዛሬ ተቋቁሟል፡፡

የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሰሜን አሜሪካ ከሕዝብ ጋር ባካሄዷቸው ምክክሮች ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ አልማን በዘላቂነት መደገፍና ለዚህም የሚያመች አሰራር እንዲኖር ማድረግ ነበር፡፡ በዚህም ምክክር በተደረገባቸው ግዛቶች ሁሉ ጊዜያዊ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ ወደ ቋሚነት እየተቀየሩ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ዛሬ ታኅሳስ 19/2012 ዓ.ም የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የአልማ አደረጃጀት ተመሥርቷል፡፡ መዋቅሩን ለሁለት ዓመታት የሚመሩ 15 ግለሰቦችም ተመርጠዋል፡፡

የኮሚቴ አባላቱ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖች በቋሚነት በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ 120 ዶላር ለአልማ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በሌሎችም ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ እንዲያደርጉ የታሰበውን ተሳትፎ ቀጣይነት ባለው መልኩ የማስተባበር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡

በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ወገኖች በአማራ ክልል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና ልማት ዕውን እንዲሆን የታሰበውን የተቀናጀ ተሳትፎ በማስተባበር በኩልም ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ታምኗል፡፡

በሌሎች የሰሜን አሜሪካ ግዛቶችም በተመሳሰይ መልኩ ጊዜያዊ አደረጃጀቶች ወደ ቋሚነት እንደሚቀየሩ መርሀ ግብሩ ያሳያል፡፡

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በአማራ ክልል የዳስ ትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየር የሚያግዝ ገቢ ለማሰባሰብ የሙዚቃ ዝግጅት እና የእራት ግብዣ መርሀ ግብር ይካሄዳል፡፡ በዝግጅቱም ታዋቂ አርቲስቶች የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፤ ምሁራን፣ ባለሃብቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችም በክብር እንግድነት እንደሚገኙ መርሀ ግብሩ ያሳያል፡፡

ዘጋቢ፡- አስማማው በቀለ-ከዋሽንግተን ዲሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here