በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ21 ሺህ በላይ ተማሪዎች አልተመዘገቡም ተባለ፡፡

0
29

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 03/2012 ዓ.ም (አብመድ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩና መረጃ ከተሠራላቸው ውስጥ 21 ሺህ ተማሪዎች በ2012 ዓ.ም አልተመዘገቡም ተብሏል፡፡

ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም 4ኛ ዙር 7ኛ ዓመት 4ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ያካሄደው ምክር ቤቱ የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ምዝገባን ገምግሟል፡፡ በተለይም በ2011 ዓ.ም በትምህርት ገበታ ላይ ቆይተው እና ‹ሮስተር› ተሰርቶላቸው የነበሩ ከ21 ሺህ በላይ ተማሪዎች በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አለመመዝገባቸውን በጉድለት አንስቶ ተወያይቷል፡፡

አብመድ የምክር ቤቱን ሐሳብ ይዞ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያን አነጋግሯል፡፡ ‹‹የ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ካለፉት ጊዜያት የተለየ ነበር›› ያሉት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገብረሕይወት አዱኛ የዘንድሮው የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ በተወሰኑ ጊዜያት (ከመስከረም 6 እስከ መስከረም 18 መጠናቀቁ ለችግሩ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ከዚህ ቀደም በነበረው የተማሪዎች ምዝገባ ልምድ እስከ ጥቅምት እና ሕዳር ወራት ይቀጥል ነበር፤ ወላጆች በዚያ የሚቀጥል ስለመሰላቸው በርካታ ተማሪዎች አልተመዘገቡም ተብሏል፡፡ ወላጆች እስካሁንም ድረስ ልጆቻቸው እንዲመዘገቡ እየጠየቁ ቢሆኑም ‹‹ለትምህርት ጥራት ሲባል ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውጭ ምዝገባ ማስተናገድ አልተቻለም›› ተብሏል፡፡

ከመምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በብሔረሰብ አስተዳደሩ 264 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የተማሪዎች እቅድ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ይዞ ትምህርት ተጀምሯል፡፡

መምሪያው የተማሪዎችን የትምህርት ግብዓት እና ቁሳቁስ ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አቶ ገብረሕይወት ተናግረዋል፡፡ በዚህም የመማሪያ መጻሕፍት ሕትመት፣ የትምህርት ቤት ደረጃ ማሻሻል፣ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የኮሙዪኒኬሽን ዳይሬክተር ጌታቸው ቢያዝን ለአብመድ በሰጡት ምላሽ ‹‹በትምህርት የጊዜ ሰሌዳው መሠረት ከተቀመጠው የምዝገባ ጊዜ ውጭ ተማሪዎች እንዳይስተናገዱ አቅጣጫ ተቀምጧል፤ መረጃው ተጣርቶ ያልተመዘገቡ ተማሪዎች በቀጣይ ዓመት እንዲመዘገቡና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል›› ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here