በውጭ ሀገራት የሚኖሩ አማራዎች ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት በተቀናጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ አቀረቡ።

0
15

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ አማራዎች ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት በተቀናጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጥሪ አቀረቡ።

በአማራ ክልል ኢንቨስትመንት፣ ልማት እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ሜሪላንድ ላይ እየተካሄደ ነው፡፡

የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ከሚኖሩ አማራዎች እና የአማራ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያዩ ነው። ውይይቱ “የአማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ መልዕክት ነው በሜሪላንድ-ሲልቨር ስፕሪንግ የተጀመረው።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው በዋሽንግተን ዲሲ፣ ቨርጂኒያ፣ ሜሪላንድ እና በልቲሞር ከሚኖሩ አማራዎች እና የአማራ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ኢትዮጵያውያን ጋር እየተወያዩ የሚገኙት።

አቶ ዮሐንስ ለተወያዮቹ ባስተላለፉት መልዕክት በአማራው እና በሀገር ህልውና ላይ ሁሉም የጋራ አቋም ሊይዝ ይገባል ብለዋል። በመሆኑም አንድነትን ለማጠናከር እንጂ ለመለያዬት መሥራት እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

በክልሉ ኢንቨስትመንት እና ልማት በተደራጀ መልኩ እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡት ደግሞ አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው። ለአብነትም በአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ በአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) እንዲሁም ወደ ፊት በሚቋቋመው አማራ ኢንሹራንስ በመሳተፍ እራሳቸውንም፣ ሕዝቡንም እንዲጠቅሙ ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የጠየቁት።

አልማ ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ከባላት ቢኖሩትም በውጭ ሀገራት ያሉት አባላት ጥቂት በመሆናቸው ማኅበሩን በመደገፍ የክልሉን የትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ልማት እንዲያፋጥኑም አቶ መላኩ አስገንዝበዋቸዋል። አልማ በሶስት ዓመታት የለውጥ ዕቅዱ ከውጭ ሀገራት አባላቱ በዓመት በአማካይ 120 ዶላር ለማሰባሰብ ማቀዱ ይታወሳል።

በዚህ ውይይት ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

ከዛሬው ውይይት አስቀድሞ የሥራ ኃላፊዎቹ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ከሚኖሩ ከባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ የሙያ ማኅበራት እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ጋር በየዘርፉ ሲመክሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

ዘጋቢ፦ አስማማው በቀለ – ከሜሪላንድ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here