“በየደረጃው ያለን የመንግሥት አካላት በትኩረት ባለመሥራታችን የተወሰኑ ግለሰቦች ግንባታውን እያወኩ ነው፡፡” ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ አያሌው

0
101

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 26/2012ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን በሚሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች በመምከር የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ውይይት ተደርጓል፡፡

በአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ አያሌው መሪነት በፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መሠረተ ልማቶች ከሚገነቡባቸው አካባቢዎች የዞን እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ ተቋራጮች፣ የግንባታ አስተባባሪዎች፣ የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የመንገዶች ባለስልጣን ተወካዮች እና የወሰን ማስከበር ባለሙያዎች የተካተቱበት ውይይት ነው ትናንት ምሽት የተካሄደው፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሰሜን ቀጣና (ሪጂን) አስተዳድር ፋይናንስ የወሰን ማስከበር ቡድን መሪ አቶ ነብዩ ተስፋዬ ባቀረቡት የመነሻ ሐሳብ በክልሉ በ12 ነባር እና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ችግሮች መጋረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ በመንገድ ፕሮጀክት ወሰኖች ላይ ሕገ-ወጥ ቤት መገንባት፣ አትክልት መትከል እና ማረስ በመሠረታዊነት የተነሱ ችግሮች ናቸው፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥት አካላትም ጭምር በሕገ ወጥ ግንባታ እየተሳተፉ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የወሰን ማስከበር፣ የተቋራጮች አቅም ማነስ፣ የካሳ ግምት ሰነዶችን ፈጥኖ ሠርቶ ለፌዴራል መንግሥት አለመላክ እንዲሁም ካሳ የተከፈለባቸውን የመብራት፣ የቴሌኮም እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን አለማንሳት እና ሌሎችም በፕሮጀክቶች ላይ የተጋረጡ መሠረታዊ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች በአስቸኳይ በመፍታት ለተቋራጮች ክፍት እንዲሆኑ ማድረግና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ መሥራት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡ የካሳ ገማች ኮሚቴዎች ኃላፊነታቸውን በሚገባ እየተወጡ አለመሆኑን በማመላከትም አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዞን እና የወረዳ አስተዳዳሪዎችም የተነሱትን ችግሮች በአጭር ጊዜ ለመፍታት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥት ክፍተቶች እንዳሉበት ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ ወረዳዎች እና ዞኖች ሥራቸውን ቢያጠናቅቁም ከመንገዶች ባለስልጣን በኩል ከፍተኛ መዘግየት መኖሩን አንስተዋል፡፡ የግንባታ ተቋራጮች የአቅም ውስንነት እና የግንባታ ጥራት ችግርም ከተሳታፊዎቹ በስፋት ከተነሱት መካከል ናቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ችግሮቹ እንዲቀረፉ እና በግንባታ ጥራት እና ፍጥነት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በቅርበት እንዲከታተል ጠይቀዋል፡፡
በባለስልጣኑ የፕሮጀክት ኮንስትራክሽን ከፍተኛ አማካሪ አቶ ተፈራ ዋቅሹም እንደገለጹት ደግሞ የመንገድ ጥራት ችግር የፌዴራል መንግሥቱ ትኩረት በመሆኑ በትኩረት የሚከታተል ዳይሬክቶሬት መቋቋሙን አመላክተዋል፡፡ የግንባታ አማካሪዎችም በትኩረት እየሠሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ አያሌው ‹‹የክልሉ ሕዝብ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ጥያቄ አለው፣ በየደረጃው ያለን የመንግሥት አካላት በትኩረት ባለመሥራታችን የተወሰኑ ግለሰቦች ግንባታውን እያወኩ ነው›› ብለዋል፡፡ ኮንትራክተሮችም የመንግሥትን እና የሕዝቡን ድክመት ተጠቅመው በተገቢው መንገድ እየሠሩ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ለተነሱት ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈለግላቸውም አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡ የግንባታ ፍጥነትን እና የጥራት ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ሆኖ መከታተል እና መጠየቅ እንደሚገባውም ነው አቶ ላቀ ያሳሰቡት፡፡

የመሠረተ ልማት ጥያቄ ያለውን ሕዝብ ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት እንዲከታተል በማድረግ የግንባታ መጓተትን መከላከል እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንም የሚነሱበትን ቅሬታዎች በመፍታት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here