ብሔር ተኮር የፌዴራሊዝም ሥርዓት በሀገሪቱ ለሚታየው አለመረጋጋት ዋነኛ መንስኤ መሆኑ ተገለጸ፡፡

0
50

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 27/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን በውይይት መፍታት ካልተቻለ መጭውን ጊዜ አሳሳቢ ሊያደርገው እንደሚችልም ተሰግቷል፡፡ ለመሆኑ ያለው አለመረጋጋት ዓብይ መንስኤና መፍትሔዎቹ በምሁራን እይታ ምን ይመስላሉ? እና ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሠላምና ደኅንነት ትምህርት ክፍል አስተማሪ ከሆኑት መምህር ያሬድ ደበበ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

እንደ መምህር ያሬድ ማብራሪያ ግጭት በግለሰቦች፣ በቡድኖችና በሀገር ደረጃ ሊከሰት የሚችል ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ የነበረ፣ ያለና ወደ ፊት ሊቀጥል የሚችል ጉዳይም ነው፡፡ በሰዎች ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ በግለሰቦች መካከል የሐሳብ ልዩነት መኖሩ፣ ቡድኖች በግጦሽ መሬትና በመሰል የጋራ ጥቅም ቅራኔ መፍጠራቸው፣ ሀገራት ከወራሪዎች ራሳቸውን ለመከላከል የከፋ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ መሆኑን ከኢትዮጵያ ባለፈ ከዓለም ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹በግጭትና ውጤቱ ላይ ማላዘን ብቻ ሳይሆን ወደ ሠላም ሂደት የሚወስደውን ትክክለኛ መንገድ መከተል የመፍትሔው ዋነኛ አካል ነው›› ብለዋል መምህሩ፡፡ ለዚህም ወደ ግጭት ሊያስገቡ የሚችሉ አንኳር ጉዳዮችን ቀድሞ መረዳት ተገቢነት እንዳለውም መክረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ “በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እየታዩ ያሉ ግጭቶች መነሻቸው ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለዩ ናቸው” ብለዋል መምህር ያሬድ፡፡ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ተግባራዊ የሆነው የብሔር ተኮር የፌዴራሊዝም ሥርዓት ዋነኛ የሀገሪቱ ሕዝብ የግጭት መንስኤ እየሆነ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ ሥርዓቱ በሕገ መንግሥቱና በሌሎች የሕግ ማዕቀፎች ከለላ እንዲያገኝ ተደርጎ በመኮትኮቱም የዘውግ አስተሳሰቦች እንዲያብቡና “የኔ ብቻ” የሚለው አስተሳሰብ እንዲያፈራ በር ከፍቷል ተብሏል፡፡ ለረዥም ዓመታት ሕዝቡ ጥያቄ እያቀረበባቸው መልስ ያላገኙ ያለ ምንም እልባት ሲንከባለሉ የቆዩ የወሰንና የማንነት፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳዮች የግጭት መንስኤዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ደካማ የተቋማት አደረጃጀት መኖሩን ሌላኛው የግጭት መንስኤ አድርገው ባለሙያው ሐሳብ ሰጥተውበታል፡፡ የመንግሥት ሥርዓቱ የደርግ መንግሥት ሥርዓትን ገርስሶ ራሱን ሲተካ ያለፈውን ሥርዓት መልካም ሥራዎች ጥሎ ከዜሮ ጀምሮ በአዲስ መዘርጋቱም ለድክመቱ መንስኤ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ በየትኛውም አካባቢ ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ዓላማ ሰንቀው የተቋቋሙ ማኅበራዊ፣ ፖለተካዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ወገን ተኮር አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹አብዛኛዎቹ ተቋማት የብዙኃኑን ሳይሆን የግለሰቦችን ጥቅምና ፍላጎት ማስተናገጃ ናቸው፡፡

የዘመድ አዝማድ፣ የትውውቅና የዘውግ ወገንተኝነት አሰራርርን ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ የሚያስገድድ በመሆኑ ልዩነቱ እንዲሰፋ አድርጓል›› ነው ያሉት፡፡ ግጭቶች ሲፈጠሩ ለችግሮች መፍትሔ የሚያስቀምጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ድርሻ መቀዛቀዝ በየቦታው የሚነሱ ቅራኔዎች እልባት እንዳያገኙ አስተዋጽኦ ማድረጉም ነው የተመላከተው፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በዚህ ወቅት ግጭት ከማብረድ ያለፈ ሥራ እያከናወኑ አለመሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡ እንደ ምሁሩ ማብራሪያ የተጠቀሱት አካላት አሁን ላይ ተሰሚነታቸውም ሆነ ሚናቸው ዝቅተኛ እየሆነ ነው፡፡ አብዛኞቹ ገለልተኛና ችግሩ እልባት እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ውስንነት እንደሚታይባቸውም ነው ምሁሩ ያመላከቱት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ (ዶክተር) ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ “ለውጥ መጥቷል” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮም ብሔርን መሠረት ያደረገ የፌዴራል አወቃቀሩ የፈጠረው ክስተት የብሔር ተኮር ግጭቶችን ጡዘት ላይ እንዳደረሰው ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ ለመረዳዳት ይውል የነበረው ደቦ ባሕላዊ እሴት በጥፋት ተቀይሮ ማኅበራዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

የደቦ ፍርድ የሚሰጡ ኢ- መደበኛ የብሔር አደረጃጀቶች የመንጋ ፍርድ እንዲሰጡ እያደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም የተጠቀሱትን ዋና ዋና ያለመረጋጋት መንስኤዎች የሚመለከታቸው ሁሉ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ መፍታት እንደሚጠበቅባቸው ባለሙያው መክረዋል፡፡ በሀገሪቱ ዋና ዋና የግጭት መንስኤዎችና እያስከተሉት ስላለው ጥፋት ሕዝባዊ ውይይት ማድረግ በመካካለኛ የጊዜ ሰሌዳ ሊሠራ የሚችል ተግባር እንደሆነም ነው ባለሙያው ያስቀመጡት፡፡ በዚህ ወቅት ያለው ችግር ዋነኛ መንስኤ የዘውግ ፖለቲካ ያመጣው ውጤት በመሆኑ ውይይቱ “ዘውጉን ወከልን” ከሚሉ ምሁራን መጀመር እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡ ቀጥሎም ሕዝባዊ ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ መድረስ ይገባልም ብለዋል፡፡ መንግሥት የብሔር ፌዴራሊዝን ወደ መልክአ ምድራዊ ፌዴራሊዝም መቀየር ካልቻለም የሠላም እጦት ችግሮቹ ሊቀጥሉ የሚችሉ መሆኑን ማጤን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ሕዝቡን በይበልጥ ወደ ግጭት እያስገቡት ያሉ፣ በቀጣይም ጥያቄ ሊያስነሱ የሚችሉ ነባራዊ የመልማት ጥያቄዎችንና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው መምህር ያሬድ ያመላከቱት፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here