“ተረት እስኪመስል ድረስ በጣም የምንኮራባቸውን እሴቶቻችንን አጥተናቸዋል”

0
251

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 04/2012 ዓ/ም (አብመድ) የተወለዱት በቀድሞው ጐጃም ጠቅላይ ግዛት አገው ምድር አውራጃ ዳንጊያ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። በልጅነታቸው በቤተክህነት ፊደል መቁጠር ጀመሩ:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ዳንግላ ከተማ በቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በደብረማርቆስ ከተማ በንጉሥ ተክለሃይማኖት ትምህርት ቤት አጠናቀዋል:: በአዲስ አበባ እና በሩሲያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል::

በሩሲያ ሞስኮ ለሰባት ዓመታት የአማርኛ ሬዲዮ አዘጋጅ ሆነው ሰርተዋል:: ለአገራችን የኪነ ጥበብ እድገት ቁልፍ ሚና ያለውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከልን ያቋቋሙም ሰው ናቸው:: የህዝብ ለህዝብ የአውሮፓ ጉዞ ደራሲም ናቸው:: ከዚህ ባለፈ በርካታ ድርሰቶችንና የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለህዝብም አቅርበዋል:: በአሁኑ ሰዓትም ከኪነጥበቡ ዓለም ሳይርቁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ላይ እያገለገሉ ይገኛሉ:: የዛሬው የበኩር እንግዳዬ አንጋፋው ከያኒ የተውኔት፣ የግጥም፣… ደራሲ እና መምህር ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ናቸው::

በመጀመሪያ እንግዳ ስለሆኑኝ እጅግ አመሰግናለሁ!
አገር አቋርጣችሁ እዚህ ድረስ በመምጣት እንግዳ ስላደረጋችሁኝ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በኩር ጋዜጣን እጅግ አመሰግናለሁ!

አገራችን ኢትዮጵያ የራሷ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት እና እውቀት ያላት አገር ናት:: ነገር ግን የራሳችን ማንነት ላይ ከማተኮር የልቅ የውጪውን ዓለም የመናፈቅ ነገር ይታያል:: እርስዎ ይህን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
ይህንን የሚያደርገው ሁሉም ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ቀዳሚ ጉዳይ ነው:: በዘመናዊ ትምህርት ታንፆ የወጣው ወጣት አለ:: ነባር እውቀቱን መሰረት በማድረግና ተሀድሶን በማግኘት ዘመናዊ የሆነ ትውልድም አለ:: ሁለቱ የተለያዩ ናቸው::
የራሳቸው የአኗኗር ዘይቤም ያላቸው ናቸው:: የከተማውን ልጅ ስናይ በዘመናዊ አስኳላ የታነፀው ወጣት ከልጅነቱ ነው የሚጀምረው:: ይህ የሚሆንበትም ምክንያት አንድም በቤተሰቡ ውስጥ ያለው የአባትና የእናት ግንኙነት የላላ ስለሚሆን ነው:: ከዚህ ባለፈም ከቤተሰቦቹ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች የሚወያዩበት የሚማማሩበትና ሀሳብ የሚለዋወጡበት መድረክ አናሳ ነው:: ስለሆነም ልጆቹ ቀኑን ሙሉ ትምህርት ቤት ይውላሉ፤ ቤተሰብ ሥራ ውሎ እና አምሽቶ ይገባል:: በዚህ ምክንያት ሊገናኙ አይችሉም:: ታዲያ በዚህ ዓይነት ህይወት ውስጥ ያለው አብዛኛው የአስኳላ ተማሪ ከላይ የጠቀስናቸውን ባህል ማንነት፣ ወግና ልምድ አለማክበር የውጪውን ነገር መናፈቅ ባህሪ ማምጣትና የኢትዮጵያዊነት እሴትን ይዞ ያለማደግ ችግር ቢኖርበት ብዙም ሊያስደነግጠን አይችልም::

Image may contain: 1 person, smiling, suit
ቤተሰቡም ቢሆን ያልዘራውን ሊያጭድ አይችልም:: መጀመሪያ ዋናውን መሠረት አስተካክሎ ማሳደግ ይገባ ነበር:: ትምህርት ቤቶችም ቢሆኑ ከዚህ የባሱ ናቸው:: ማንነትና ኢትዮጵያዊነት ላይ ከማተኮር ይልቅ የሰውን መናፈቅ፣ ሌላውን መሆን ላይ ስለሚያተኩሩ ክፍተቱ የሰፋ እና አሳሳቢ እንዲሆን አድርጐታል::
ኢትዮጵያዊነት እና የአገር ፍቅር የሚባሉት ነገሮች መጀመሪያም የሚወረሱት ከእናት ጡት ነው:: የእናቱን ጡት እየጠባ ትንፋሿን እየሳበ የደረቷን ሙቀት እያገኘ ያላደገ ህፃን እንዴት ለአገሩ ፍቅር ሊኖረው ይችላል? ዋናው መሠረቱ ይህ ነው:: ይህንን ሳታደርግ ልጅን በሞግዚት ብቻ የምታሳድግ እናት ልጇን ፍቅር ስጠኝ፣ አገርህን ውደድ ብትል ከየት ያየውንና ያገኘውን ሊያደርግ ይችላል:: ስለዚህ ይህን ስንል ሁሉም ያደርጋል ማለት ባይሆንም አሁንም ልጆቻቸውን በአግባቡ ቀርፀው የእናትና የቤተሰብ ፍቅር ሰጥተው ለቁም ነገር የሚያበቁ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ መዘንጋት አይኖርብንም::
አምጣ ያልወለደችው ልጅ፣ ጡት ሳታጠባ ያሳደገችው ፍሬዋ ጀርባዋን ያልቀመሰው የአብራኳ ክፋይ እንዴትስ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል:: ስለዚህ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዎች እኛው ራሳችን ወላጆች ነን:: ወደ ራሳችን መሰረታችን ልንመለስ ይገባናል:: ልጆቻችን እኛን ሆነው እንዲኖሩ ማድረግ የምንችለው እኛው ራሳችን ነን:: ቁልፉ ያለውም በእጃችን ነው:: ይህን ሥራ ጊዜ ሰጥተን የምንተወውም አይደለም::

አሁን በአገራችን ላይ እየተስተዋለ ያለውን የባህል ወረርሽኝስ እንዴት ታዘቡት?
ይህ ወረርሽኝ ለእኛ አገር ብቻ ተመርጦ የተሰጠ አይደለም:: የዓለም እድገት በጨመረ ቁጥር ሁሉንም አገሮች እያጥለቀለቀ ያለ በሽታ ነው:: ሁሉም አገሮች ደግሞ ይህንን ወረርሽኝ የሚዋጉበት ግንብ ነበራቸው:: ነገር ግን ይህንን ግንብ ሊጠቀሙበት አልቻሉም:: ንፋስ በነፈሰ ቁጥር ሰነፎች ግንብ ይሰራሉ፤ ጐበዞች ግን የንፋስ ወፍጮ ይተክላሉ:: ማድረግ ያቃተን ይህንን ነው:: ስለዚህ አሁን እያየነው ያለው የዓለም ስልጣኔ መልካም ጐን እንዳለው ሁሉ በዚያው ልክ እያመጣብን ያለው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም::
ሌሎች ያደጉ አገሮችን ብናይ እነ ቻይና፣ ኮሪያ እና ጃፓን የሰሩት ሥራ አለ፤ መሠረቱን ባህላዊ አድርገው በማፅናት እና ትልቅ መሠረት ላይም በማቆማቸው ችግርን ለመቋቋም ችለዋል:: ወደ እኛ አገር ስንመጣ ትልቁ ችግራችን ምንድን ነው መሰረታችን የፀና አይደለም:: ትንሽ ነፋስ የሚያፈርሰው ነው:: ይህ ማለት ግን የለንም ወይም አልነበረንም ማለት አይደለም:: በጣም ጠንካራ የሆነ የባህል መሰረት ነበረን፤ ያንን መሰረት ንደነዋል::
ይህ ስለሆነም ወጣቱ ትውልድ ዛሬ ላይ የሚመክትበት ጋሻ ሊያገኝ አልቻለም:: ጋሻውን ነጥቀን ግንቡን ንደንበታል:: ስለዚህ ይህንን ሊቋቋም የማይችል ትውልድና ባህል ይዘን እስከምን ድረስ ልንጓዝ እንችላለን፣ አገራችንንስ እንዴት ከፍ ባለ የባህል አውድ ውስጥ እናስቀምጣታለን የሚለው ሀሳብም እጅግ አሳሳቢ የሆነ አገራዊ አጀንዳችን ነው:: ዛሬ ላይ ጠንካራ የአውሮፓ ነፋስ በአገራችን ላይ ነፍሶ ባህላችንን እየተነጠቅን እንገኛለን:: ስለዚህ ለችግሩ መፍትሔ ምንድን ነው? በምንስ ሁኔታ ከዚህ ችግር እንውጣ? የሚለው ጉዳይ ለእኔም መልስ ያላገኘሁለት ትልቅ ጥያቄ ሆኖብኛል::

“በኢትዮጵያ አተያይ የውጩን ዓለም እውቀት መጨመር ይቻላል:: ከኤቢሲዲ ወደ አቡጊዳ መመለስ ያስፈልጋል” ሲሉ ይደመጣሉ:: ይህን ለማድረግ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ምን ሊደረግ ይገባል ይላሉ?
በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያለውን በሙሉ አፍርሰን ሌላ አዲስ ነገር እንገንባ ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው:: ያም ሆኖ ግን እንደኔ ሀሳብ ለአብነት ያክል ቤተክርስቲያንን ብናይ ብዙ መሠረት ያላት በተለይም በግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ያለው እውቀት ቀላል የሚባል አይደለም:: ዛሬ ላይ ያቃተን ዋናው እና ትልቁ ነገርም ያለንን ሀብት የመጠቀም ችግር ነው::
እንደ እኔ ሀሳብና አመለካከት መንግስትም ገብቶበት የቤተክርስቲያን ሊቃውንትም አምነውበት ሌሎች የእምነት ተቋማትም ተሳትፈውበት በጋራ ወጥ የሆነ እና ሁሉንም ያሳተፈና ያማከለ የኢትዮጵያን መሠረት የሚደግፍና የሚያፀና ታላቅ የትምህርት ተቋም መመስረት አለበት። በግዕዝ ጥበብ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ከሃይማኖት ትምህርት የወጣ በእውቀትና በጥበብ ሥራ፣ በፍልስፍናና በምርምር ላይ ያተኮረ የትምህርት ሥርዓትን መገንባት ይቻላል የሚል ሀሳብ አለኝ::
የራሳችንን ቋንቋ ይዘን ከአቡጊዳ ጀምረን ህፃናት ልጆችን ከልጅነታቸው ጀምሮ በራሳቸው ባህል ወግ እና ሥርዓት እያነጽን የምናመጣቸው ከሆነ ከሚነሱት የተለያዩ ችግሮች ራሳችንንም ሆነ አገራችንን ጠብቀን የተሻልን የመሆን ዕድላችን የሰፋና ያማረ ይሆናል:: ስለዚህ ከአፀደ ህፃናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት በአግባቡ ተዋቅሮ ከተሰራ ለመምህራኑና ለሠራተኛውም ተገቢውን ክብርና ድጋፍ ካደረግን ኢትዮጵያዊ የሆነ ትምህርትን የማናስፋፋበት ምክንያት ሊኖረን አይችልም:: ስለዚህ እዚህ ላይ ሁሉም ሰው ሊረባረብና ሊሰራ ይገባል:: ይህ ሲሆን ቀደም ብለው የሚነሱ ከባህል የማፈንገጥ ራስን ያለመሆን እና መሰል ችግሮችን የመቅረፍ ምንጮቻቸውን የማድረቅ የአገርንም ዝናና ክብር ከፍአድርጎ የመሄዱ ነገር የበለጠ ያማረ ይሆናል::

ብዙ ጊዜ “በግዕዝ እንደመጠበብ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠበብ የማያኮራኝ የአባቶቼ ቋንቋና ጥበብ ናፋቂ ነኝ” ይላሉ:: ለዚህ ምክንያትዎ ምን ይሆን?
ይህን ሁልጊዜ የማነሳው ሀሳብ ነው:: እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ:: ያውም የታላቅ ህዝብ የዘር ግንድ ያለኝ ኩሩ ኢትዮጵያዊ! ለዚህም ነው ለአገሬ፣ ለህዝቤ፣ ለቋንቋዬና ለማንነቴ ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ የምሰጠው! ብችልና ባውቅ እውቀቱ ቢኖረኝ ብዙ ነገሮችን በግዕዝ ብጠበብ፣ ብተነትንና ባብራራ ደስ ባለኝ ነበር:: በግዕዝ የምታነባቸውና የምታውቃቸው ነገሮች ሁሉ አጀብ የሚያሰኙ ታላቅ ምስጢርን የያዙ እውቀቶች አሉ:: በእኔ አተያይ እና አገላለጽም በግዕዝ ቋንቋ የምትጠበበውን ያህል በየትኛውም ቋንቋ መጠበብ አትችልም:: የግዕዝ ቋንቋ ታላቅነትም ሰፊ ነው:: ቋንቋው እጅግ ጥልቅና ረቂቅም ስለሆነ፤ በግሌ ያለኝ ፍላጐት ሰፊ እና ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ከሁሉም ቋንቋ የበለጠ በግዕዝ ቋንቋ መጠበብ እና አንዳች ነገርን መስራት ብችል ደስ ይለኛል:: ይህም የአገሬን ሀብታምነትና ባለፀጋነትም ያሳያል:: ያጣነው የጐደለን ምንም ነገር እንደሌላ ቋንቋችን ብቻ በራሱ ዋና ምስክር ነው:: የእኔም ዋና ምክንያቴ ይህ ነው::

የድሮው ማህበራዊ እሴት መገንቢያ ትውፊቶቻችን ዛሬ ላይ አሉ ለማለት አያስደፈርም:: ከዚህ ችግርስ እንዴት መውጣት ይቻላል?
የኖርንባቸው መልካም የሆኑ ማህበራዊ እሴቶቻችን እየጠፉ እና እያጣናቸው ስለመሆኑ እማኝ መጥቀስ አያስፈልግም:: ቀደም ባለው ጊዜ ስናይ ከአንድ ግዛት ወደ አንዱ ለማለፍ አስፈቅዶ ከቻለም ጐራ ብሎ እህል ውሃ ቀምሶ ፈቃድ ተሰጥቶት ያልፋል:: ይህ እና መሰል መልካም የሆኑ የመተሳሰብ ባህላዊ የአኗናር ዘይቤዎች ነበሩን::
አንድ የማልረሳውና የማስታውሰውን ነገር ልንገርህ ልጅ እያለሁ፣ “በሌጣ ፈረሰ ስጋልብ አንድ ትልቅ ሰው እየመጡ አቋርጫቸው አለፍኩ:: ይህን ያደረግኩት በወቅቱ ባለማወቄ ነበር:: ያም ሆኖ ሰውየው ማንነቴን አረጋግጠው አባቴ ቤት ድረስ ሄደው እኔም ተጠርቼ እንዴት መንገድ ቆርጦኝ ይሄዳል ተብዬ ትልቅ ተግሳፅ ደረሰብኝ:: ይህንን መቼም አልረሳውም፤ ጠቅሞኛል:: ሰው እንዳከብር አድርጐኛል:: ይህንን እሴት ነው ዛሬ ያጣነው::
ሌላው በህግ ዓለም ውስጥ ስትሄድ ሰው ከሰው ጋር እየተጣላ ተጋምሶ ደምቶ እየተደባደበ ለመገላገል ገብተህ በህግ አምላክ ስትል ወዲያው ሁለቱም ያቆማሉ:: ሰውየው ከቻለ ያስማማል፤ ካልቻለ ወደ ህግ ቦታ ይወስዳል:: ይህ በእኔ ህይወት ውስጥ ያየሁት ነው:: ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣና ሲወርድ የነበረው ሥርዓት እጅግ የተለየ እና ታላቅ ፍቅርም የሚታይበት ሁኔታ ነበር:: ዛሬስ ስንል ይህ ሁሉ ታሪክ እየሆነ ሁሉም ነገር ተረት እስኪመስል ድረስ በጣም በርካታ የሆኑትን የምንኮራባቸውን እሴቶቻችንን አጥተናቸዋል::
ግብረገቡን፣ መተሳሰቡን፣ የሽምግልና ሥርዓቱን ሁሉ አልተጠቀምንበትም፤ ይህ ያሳዝነኛል:: ዛሬ ላይ እንኳን የሰው ልጅ ልትቀጣ ቀርቶ ቃል አውጥተህ መናገርም አትችልም:: ይህ ሁሉ እሴቶቻችን እንደተበላሹ እያሳዩን ነው:: ስለዚህ ማህበራዊ እሴት መገንቢያ የሆኑትን ታላቅ ትውፊቶቻችንን ማጠናከርና ኢትዮጵያዊ እሴትን መገንባትም ሆነ ይዞ የመቀጠል ሥራ ከሁላችንም ይጠበቅብናል፤ መንግስትም በትኩረት ሊሰራበት እና ዳግም ትንሳኤውን ለማብሰር በመጣር ትልቅ አጀንዳም ሊያደርገው ይገባል የሚል ሀሳብ አለኝ::

አሁን ያለውን የአገራችንን የፖለቲካ ሥርዓት እንዴት ያዩታል?
ቀደም ባለው ጊዜ ጐጃም ውስጥ ቆምጨ አምባው የሚባል ሰው ነበር:: እናም ይህንን ሰው በዘመነ አብዮት ማርክስና ሌኒን እንዴት አየሀቸው ቢሉት አሉ እንደ በላይ ዘለቀ አለ:: ሌላው ደግሞ ኢምፒሪያሊዝምን እንዴት አየኸው ቢሉት የጐሪጥ አለ:: እንግዲህ ይህ ሁሉ አሉ ነው:: እናም እኔ የዛሬውን ለውጥ የጐሪጥ አይደለም የማየው ቀጥታ ፊት ለፊት ነው የማየው::
እውነት ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ (ዶ/ር) ይህንን ለውጥ አድርጐ የሚፈለገውን የምርጫ ሥርዓት አምጥቶ አንዲት ጥይት ሳትተኮስ ምርጫ ተካሂዶ አሸናፊው ፓርቲ ስልጣን ይዞ እሚያሳየን ከሆነ አብይ በዚህ ምርጫ ቢሸነፍም፤ ባይሸነፍም በዜሮም ቢወጣ የአሸናፊዎች አሸናፊ ተብሎ የሚጣራ ሰው ይሆናል:: እናም ይህንን ማድረግ እንዲችል ምን እናድርግለት የሚለው ጥያቄ ዋና ጉዳይ መሆን ይገባዋል:: በእርግጥ በየቦታው የተለያዩ ችግሮች እናያለን፤ እንሰማለት፤ እናዝናለን:: ይህ ታፍኖ የኖረ ችግር በመሆኑ የሚከሰት ነው:: በእርግጥ ሁኔታው ውስጥህን ይጐዳሀል ያም ቢሆን ጠንካራ ሆኖ መቀጠል ተገቢ ነው:: ከዚህ ባለፈ ግን ለተሻለ ለውጥና ነፃነት ትልቁ መፍትሔ የሚሆነው በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራቱ ነው:: ስለዚህ ፖለቲካውን ለማስተካከልም የህዝቡን ሰላም አረጋግጦ ለመጓዝና ተናቦ፣ ተነጋግሮ ሀሳብ ለሀሳብ ተወያይቶና ተግባብቶ ማስቀጠል እንዲቻል ለማድረግ ዘወትር ያለ እረፍት መስራቱ ተገቢነት አለው:: ከዚህ ባለፈ ብዙዎች ለአገራችን ፖለቲካ መከተል ያለባቸው የዜግነት ፖለቲካ ነው:: ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው የብሔር /ዘር/ ፖለቲካን ያራምዳሉ:: ይህ እንግዲህ እንደየ ሰው አመለካከትና ፍላጐት የተለያየ ቢሆንም እንደ እኔ እምነት የብሔር ፖለቲካ የሚጠላ አይደለም:: ማነኛውም ሰው ማንነቱን ማወቁ አይከፋም:: ብሔር አያስፈልግም ማለትም አያስፈልገንም:: የምናደርገው ነገር ቢኖር መሆን ያለበት ዋናው ጉዳይ በብሔር ማንነት ውስጥ ፖለቲካን ማውጣት መቻል አለብን:: የሚያበጣብጠውም ፖለቲካ ሲገባበት ነው:: ስለዚህ ይህን አሠራር ልንከተል ይገባናል::
እኔ የሚለውን አስተሳሰብ እኛ በሚል ሀሳብ ቀይረን መሄዱ የተሻለ ነው:: ለዚች አገር ዕድገትም የዜግነት ፖለቲካ የብሔርን ማንነት ተገቢነት ባለው መንገድ አክብሮ መሄድ ከቻለ ይጣረሳሉ የሚል እምነት የለኝም:: ዋናው ግን ፖለቲካው ብሔሩን ሊገዛው ከፈለገ አደጋው የከፋ ይሆናል:: ስለዚህ አንድ ሆነን በፍቅር ተሳስበን በጋራ ልቦና አጢነን የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን አውቀን ከሰራን ፍቅራችን ሰፍቶ ልዩነታችን ጠቦ የምንዋደድ ህዝቦች ሆነን መቀጠል እንችላለን ብዬ አስባለሁ::

ስለነበረን ሰፋ ያለ ጊዜ በጣም አመሰግናለሁ!
እኔም አመሰግናለሁ ልጄ ተባረክ!

(ሰለሞን አሰፌ)
በኩር ጥቅምት 03 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here