ትናንት ከአሰልጣኝነት መንበራቸው የወረዱትን አሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬይ የሚተኩ አስልጣኝ ማን ይሆኑ የሚለው አጓጊ ሆኗል፡፡

0
17

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) ‹‹ከ18 ወራት በኋላ ከእምሬትስ የተሰናበቱት ኢምሬይን ተክተው ለንደን የሚደርሱ አሰልጣኝ ማን ይሆኑ?›› የሚለው ትኩረት ስቧል፡፡ ኢሚሬይ በራሞን ሳንቸዝ ፒዥዋን ስታዲዬም ከሀገራቸው ቡድን ሲቪያ ጋር አስደናቂ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ ሲቪያ በአውሮፓ መድረክ እንዲደምቅ አድርገዋል፡፡ በዚያ ወቅት ላላቅ የአውሮፓ ቡድኖችን የሥራ ኃላፊዎች ቀልብ ሰብው ነበር፤፡፡ ነገር ግን የፈረንሳዩን ሀብታም ቡድን ፒ ኤስ ጂ የሚቀድመው አልነበረም፡፡ ከሲቪያ አውጥቶ ወደፓሪስ ይዟቸው ኮበለለ፡፡

በፓሪስ ቆይታቸው በስታዲዮ ፓርክ ዲስ ፕሪንስ ስታዲዬም የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን ሰበሰቡ፤ ነገር ግን በአውሮፓ መድረክ የተሳካ ጊዜን አላሳለፉም ነበር፡፡ በፓሪስ ቆይታቸው ብራዚላዊውን ኮኮብ ኔማር ጁኔርን ከካታሎኑ ኃያል ባርሴሎና በማይታመን የገንዘብ መጠን ወደፓሪስ እንዲኮበልል አደረጉ፡፡ ኡናይ ኢሚሬይ በፈረንሳይ የሚዘጋጁ ዋንጫዎችን ቢሰበስቡም የሀብታሙ ቡድን የሥራ ኃላፊዎች እና ባላሀብት ግን ቡድኑ በአውሮፓ መድረክ እንዲነግሥ ይፈልጉ ነበርና ከኢሚሬይ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሻከረ፡፡ ከቡድኑ ጋርም በ2018 ተለያዩ፡፡ ኢሚሬይ ከፓሪስ ሲለቅቁ መዳረሻቸው የት ይሆን ተብሎ በጉጉት ሲጠበቅ ሥራ በለቀቁ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የአርሰን ዌንገርን ዙፋን ተረክበው ሰሜን ለንደን ደረሱ፡፡

በሲቪያና በፒ ኤስ ጂ አስደናቂ ጊዜን ያሳለፉት ኢሚሬይ ኢሚሬትስ ስታዲዬም ሲደርሱ ዋንጫ ለተጠማው አርሰናል አዲስ አብዮት ይዘው እንደሚመጡ ተስፋ ተጣለባቸው፡፡ በመጡበት የመጀመሪያ ዓመትም አርሰናል በሊጉ አራተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ሲያደርጉ በዩሮፓ ሊግ ደግሞ ለፍጻሜ አበቁት፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በማውሪዚዮ ሳሪ ሲሰለጥን በነበረው በምዕራብ ለንደን ተቀናቃኛቸው ቸልሲ ዋንጫውን ተነጥቀው ተመለሱ፡፡ ይህም ሆኖ በኢሚሬይ ተስፋ የቆረጠ አልነበረም፡፡ ይልቁንስ በሚቀጥለው የውድደር ዓመት አርሰናልን ከፍ ወዳለ ደረጃ ይስዱታል ተብሎ ተገመተ፤ ይህን ግን ማድረግ ሳይችሉ ቀሩ፡፡

በዚህም አርሰን ዌንገር ከ22 ዓመታት በላይ በቆዩበት ዙፋን ዓመታን በወራት ቁጥር እንኳ ሳይደርሱበት በተረከቡ በ18 ወራት የይልቀቁ ደብዳቤ ደረሳቸውና ተሰናበቱ፡፡ የእርሳቸውን መልቀቅ ተከትሎ ኢሚሬትን በዋና አሰልጣኝነት የሚረግጠው አሰልጣኝ ማንነት ትኩረት ስቧል፡፡ ቢቢሲ በስፖርት ዓምዱ ኢሚሬይን የሚተኩ አሰልጣኝ ማን ሊሆን ይችላል ሲል ሰፊ ሀተታ አስቀምጧል፡፡ የቀድሞው የመድፈኞቹ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ሴማን ከቢቢሲ ራዲዬ ጋር በነበረው ቆይታ ‹‹ለአርሰናል ትክክለኛው ሰው የቀድሞ አመካዩ ፓትሪክ ቪራ ነው›› ብሏል፡፡ እንዴ ዴቪድ ሴማን አስተያዬት ከሆነ ፓትሪክ ቪራ ወደ ኢሚሬትስ ቢመለስ ትክክለኛ ምርጫ ነው፡፡ አሁን በጊዜያዊነት አርሰናልን እንዲያሰለጥኑ ኃላፊነት የተሰጣቸው ፍሬዲሪክ ሉንበርግ የዋና አሰልጣኝነት ሥራውን ያገኛሉ ብሎ እንደማያምንም ዴቪድ ሴማን ተናግሯል፡፡

ከፓትሪክ ቬራ በተጨማሪ ቢቢሲ አርሰናልን በዋና አሰልጣኝነት ሊረከቡ ይችላሉ ያለቸውን አሰልጣኞች ዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የተቀመጡት የቀድሞው የጂቬንቱስ አሰልጣኝ ጣላናዊው ማሲሚላኖ አሌግሪ ናቸው፡፡ የ52 ዓመቱ አሌግሪ ከጁቬንቱስ አስቀድመው አግሊያንስ፣ ስፓል፣ ግሮሴቶ፣ ሌሶ፣ ሳሱሎ፣ ካግላሪና ኤስ ሚላንን አሰልጥነዋል፡፡ በጁቬንቱስ ቆይታቸው አስደናቂ ጊዜን ያሳለፉት አሌጊሬ አሁን እረፍት ላይ ሲገኙ አርሰናልን ሊረከቡ ይችላሉ ተብሎ ተጠብቋል፡፡

ከአሌጊሪ በመቀጠል አርሰናልን ሊረከቡ ይችላሉ ተብሎ የሚጠበቁት አሁን ላይ ወልቭስን እያሳለጠኑ የሚገኙት ፖርቹጋላዊው ኑኖ ስፒሪቶ ሳንቶ ናቸው፡፡ ሳንቶ በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ያሳኩት ዋንጫ ባይኖራቸውም በወልቪስ ቤት እያሳዩት ያለው ብቃት እንዲታጩ አድርጓቸዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አሁን በጊዜያዊነት አርሰናልን የተረከቡት ፍሬዲሪክ ሉንበርግ ናቸው፡፡ የ42 ዓመቱ ፍሬዲሪክ በአርሰናል ቤት 214 ጊዜ ተጫውተው 46 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሁለት የፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫዎችንም ከመድፈኞቹ ጋር አንስተዋል፡፡ ፍሬዲሪክ ከተጫዋችነት ባለፈም በአርሰናል ቤት ከ15 ዓመት በታችና ከ23 ዓመት በታች ቡድኑን አሰልጥነዋል፡፡ በጀርመኑ ወልፍስበርግ ለ6 ወራት ያክል ምክትል አሰልጣኝ ሆነውም አገልግለዋል፡፡

በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው የቀድሞው አማካኛቸውና የአሁኑ የፔፕ ጋርዲዮላ ምክትል አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ ነው፡፡ የ37 ዓመቱ አርቴታ አርሰን ዌንገር በ2018 ከአስልጣኝነታቸው ሲነሱ ይተካቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ወንበሩን በኢሚሬይ እንደተነጠቀ ይታወሳል፡፡

በአምስተኛ ደረጃ የተቀመጡት በቅርቡ ከሌላኛው የሰሜን ለንደኑ ቡድን ቶተንሃም የተሰናበቱት አርጀንቲናዊ ጥበበኛ መውሪሲዬ ፖቺቲኒዮ ናቸው፤ ነገር ግን ማውሮሲዮ ፖቺትኒዮ ከዚህ ቀደም ከስፔን ባርሴሎናን ከእንግሊዝ ደግሞ አርሰናልን አላሰለጥንም ማለታቸውን ተከትሎ ጭምጭምታው ላይሳካ ይችላል ተብሏል፡፡ ፖቼቲኒሆ በስፔን የካታሎኑን ስፓኞሉን ስላሰለጠኑ ሌላኛውን የካታሎን ቡድን ባርሴሎናን አላሰለጥንም ሲሉ በእንግሊዝም የቶተንሃም የምንጊዜም ተቀናቃኙ የሆነውን አርሰናልን አላሰለጥንም ማለታቸው ላሰለጠኗቸው ቡድኖች ያላቸውን ክብር ሲገልጹ ነው፡፡ ነገር ግን በእግር ኳስ ይህ አይሆንም ብሎ መገመት ከባድ ነው፡፡

የበሮንማውዙ አሰልጣኝ ኤድ ሃው፣ የናፖሊው አሰልጣኝ ካርሎ አንቾሌቲ፣ የዳሊያን ይፋንግ አሰልጣኝ ራፋ ቤኔቴዝ፣ የአያክሳም አምስተርዳሙ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ እና የሌስተር ሲቲው አሰልጣን ብሬንዳን ሮጀርስ አርሰናልን ሊያሰለጥኑ ይችላሉ ተብለው የተገመቱ ናቸው፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ
በታርቆ ክንዴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here