ትኩረት የተነፈገው አረንጓዴው ቀበቶ – ጎደቤ::

0
214

ጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ በምዕራብ ጎንደር ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ይገኛል፡፡ 18 ሺህ 690 ሄክታር መሬት ይሸፍናል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በጥብቅ ደንነት ተከልሎ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡ በ2009 ዓ.ም ደግሞ በብሔራዊ ፓርክነት ተመዝግቧል፡፡ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ ከሚገኙት  አረንጓዴው ቀበቶ (ግሪን ቤልት) እየተባሉ ከሚጠሩ የሳራ በርሃን መስፋፋት ከሚመክቱ ፓርኮች እና  የደን አካባቢዎች  ውስጥ አንዱ እንደሆነም ይነገራል፡፡  ፓርኩ ከጎንደር 237 ኪሎ ሜትር ከወረዳው መቀመጫ አብርሃጅራ ደግሞ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

አቶ መንግሥቱ ዘውዱ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡  አካባቢውን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደሚያውቁት የገለጹት አቶ መንግሥቱ ‹‹ቀደም ብሎ  ጥበቃ ባለመደረጉ በውስጡ የነበሩት እንደ ቀጭኔ፣ ውንደንቢ፣ ዝሆን፣ አንበሳ እና የመሳሰሉ እንስሳት በመጥፋታቸው ‹ነበር› ብቻ ሆኗል›› ብለዋል፡፡   በ1928ዓ.ም ጣሊያን ሀገሪቱን በወረረችበት ጊዜ ጎደቤን ለአምስት ዓመታት መቀመጫው አድርጎት እንደነበርም አቶ መንግሥቱ  አስታውሰዋል፡፡  ለአካባቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ ሰደድ አሳት፣ የእርሻ መስፋፋት እና በተለያዩ ምክንያቶች ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ዛፎች እየተቆረጡ  ደኑ የተመናመነ  እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡  መንግሥት አካባቢውን  በመጠበቅ እና በማልማት  አሁንም ፓርኩ የከፋ ችግር ውስጥ እንዳይወድቅ ማድረግ እንደሚገባውም አቶ መንግሥቱ ጠይቀዋል፡፡

የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሙያ አቶ የኔወንድም ይላቅ እንደገለጹት

በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተደረገ ጥናት በፓርኩ ውስጥ 57 የሚደርሱ የአዕዋፍ ዝርያዎች፣ 81 የዕጽዋት ዓይነቶች፣ 27 አጥቢ እንስሳት መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡  እንደ ነጭ ደርባን፣ የአፍሪካ ጥንብ አንሳ እና ‹‹ሬድ ፉትድ ሳልኮን›› የተባሉ የአዕዋፍ ዓይነቶች በፓርኩ ብቻ እንደሚገኙም ባለሙያው አስረድተዋል፡፡  ፓርኩን ከዚህ በፊት በሀገሪቱ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት በተካሄዱ እንቅስቃሴዎች ነፍጥ ያነገቡ የተለያዩ ኃይሎች መንግሥትን ለመዋጋት እና ኢትዮጵያን ከድርቡሾችና ከጣሊያን መሰል የውጭ ወራሪዎች ለመከላከል አርበኞች እንደምሽግ ይጠቀሙበት እንደነበርም ባለሙያው ነግረውናል፡፡ በውስጡም ታሪካዊ ዋሻዎች ይገኙበታል፡፡

በአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና የዱር እንስሳ ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አብርሃም ማርየ እንደተናገሩት ደግሞ ፓርኩ በውስጡ በርካታ የዱር እንስሳት እና የበርሃማነት መስፋፋትን መቋቋም የሚችሉ ዕፅዋትን የያዘ በመሆኑ ተፈጥሯዊነቱን ለማስጠበቅ በ2009 ዓ.ም በብሔራዊ ፓርክነት ተመዝግቧል፡፡

በአፍሪካ ደረጃ እየተመናመነ እንደመጣ የሚነገረው ዋሊያ መቀር፣ ለቅርፃ ቅርጽ አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውና በአፍሪካ ሀገራት በተለይም ደግሞ በኬኒያ እና ታንዛኒያ በብዛት እንደሚገኝ የሚነገረው ‹ዞቢ›፣ ቀርቃሃ  እና ሌሎች የዕፅዋት ዝርያዎች በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ደኑ የአካባቢውን ሥነ ምኅዳር ከመጠበቅ ባለፈ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዕፅዋትን የያዘም ነው፡፡

ፓርኩ  ከሚያስገኘው የቱሪዝም ጠቀሜታ ባለፈ  በውስጡ በሚፈስሱ ወንዞ ለዓሣ እርባታ፣ ዕጣን፣ ማር፣ ሽመል ምርት እና  የከብት መኖ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

የሰሃራ በረሃ ወደ ቻድ እና ሱዳን  በዓመት መቶ ኪሎ ሜትር እየሰፋ እንደነበር የገለጹት ዳይሬክተሩ በርሃማነቱ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የሚያደርገውን  መስፋፋት በዓመት ከ10 ኪሎ ሜትር ባነሰ እንዲቀንስ ለማድረግ የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክም አስተዋጽኦ ማድረጉን አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በኢትዮጵያ ምዕራባዊ ክፍል ‹አረንጓዴው መቀነት› እየተባሉ የሚጠሩት አልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ፣ የማኅበረስላሴ አንድነት ገዳም ደን፣  ጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ፣ የአንገረብ ደኖች፣  የሽመለጋራ ደኖች  እና በትግራይ ክልል የሚገኘው የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ መገኘት እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ በኢንዱስትዎች መስፋፋት ምክንያት እየጨመረ የመጣውን  የካርቦን ልቀት  በቀጥታ በማመቅ ወደ ኦክስጅን በመቀየርም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳት ስምምነት ላይ ባይደረስም የአደጉ ሀገራት በኢንስትሪዎች ለሚለቁት ካርቦን  የሥነ ምኅዳር ክፍያ ተመን ወጥቷል፡፡  ክፍያው ሀገራቱ የሚለቁትን ካርቦን ለማስወገድ የሚያወጡትን ወጭ ታሳቢ ተደርጎ ደኖችን ለሚጠብቁ ሀገሮች መክፈል እንዳለባቸው የወጣ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

አቶ አብርሃም እንደገለጹት በሀገሪቱ ያሉ ጥብቅ ደኖች የሚለቀቀውን ካርቦን  ወደ ኦክስጅን  በመቀየር  የሚያስገኙትን ገቢ ተጠንቷል፡፡  የጎደቤ ፓርክ ብቻ ካርቦንን በማመቅ በዓመት 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ በጥናት መመላከቱን  ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ልቅ ግጦሽና ሰደድ እሳት ለፓርኩ  ፈተናዎች ናቸው፡፡   በፓርኩ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ለቱሪዝም ክፍት ለማድርግ እና ለማኅበረሰቡ ጥቅም እንዲሰጡ ለማድርግ የበጀተ ችግር ትልቅ ፈተና እንደሆነም ነው አቶ አብርሃም የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here